አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደራችን ቁልፍ ተግባር ተቋም መገንባት ነው አሉ።
ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ፣ ዛሬ በተቋማት ከምንሰራቸው የሪፎርም ስራዎች በደንብ ማስከበር ባለስልጣን የተቋም ግንባታ እና የሰው ሃይል ልማት በ10 ዙር ሲሰለጥኑ የነበሩ ኦፊሰሮችን አስመርቀናል ብለዋል።
የአቅም ግንባታ ስልጠናው ኦፊሰሮቻችን ከህዝብ ጋር አክብሮት የተሞላበት ተግባቦት እንዲኖራቸው፣ ህግና ስርዓትን ያለአንዳች አድልዎ እንዲያስከብሩ፣ ፍፁም አገልጋይነት እንዲላበሱ ፣ ስነምግባር የተላበሱ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ሲሉም አመልክተዋል።
ከንቲባዋ ተቋሞቻችን በስርዓት የተገነቡ፣ ጠንካራ የአገልግሎት ስርዓት ያላቸው፤ ስነምግባር የተላበሱ እንዲሁም ለህዝብ ቅርብ የሆኑ ባለሙያ እና አመራር የመፍጠር ተቋማዊ የሪፎርም ስራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
አዲስ አበባ የዓለም ዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ፣ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች ወታደራዊ አለባበስ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን የጠበቀ እንዲሆን ሲጠቀሙበት ከነበረው የደንብ ልብስ ተጨማሪ ሆኖ የሚያገለግል አዲስ የደንብ ልብስ ይፋ መደረጉን ከንቲባዋ አስረድተዋል።
የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮቹ ሕዝብን በፍቅርና በትህትና በማገልገል፣ ሕግና ደንቦችን ደግሞ ያለምንም አድልዎና ርህራሄ ማስከበር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

