አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ያካሄደችው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ታሪካዊ መሰረት ጥሎ አልፏል አለ የአፍሪካ ኅብረት፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ማሳወቂያ መርሐ ግብር እያካሄደ ይገኛል፡፡
በኅብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር÷ ኅብረቱ የታዛቢዎች ቡድን በማሰማራት ምርጫውን መታዘቡን አንስተዋል፡፡
በቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የተመራ የኅብረቱ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን የመጀመሪያ ዙር ሪፖርት ማቅረቡን አስታውሰዋል፡፡
ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንግስትና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላደረጉት ጥረት ኅብረቱ እውቅና አንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
ምርጫው አካታች፣ ነፃ እና ፍትሐዊ እንደነበር ጠቅሰው፥ ሒደቱም በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ ታሪካዊ መሰረት ጥሎ ማለፉን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዴሞከራሲ ስርዓትና የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲጠናክሩ እንዲሁም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር የአፍሪካ ኅብረት ድጋፉ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
አፍሪካ ዴሞክራሲን ከመለማመድ ውጭ አማራች እንደሌላት የገለጹት ኮሚሽነሩ፥ በአህጉሪቱ ቅቡልነት ያለው የመንግስታት ምስረታ እንዲከናወን በትኩረት መስራቱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

