አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ከሁሉም የኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በትብብር እንቀሳቀሳለሁ አለ።
ፓርቲው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ይፋ መሆኑን ተከትሎ በሰጠው መግለጫ፥ ምርጫው በስኬት በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አለን ብሏል።
ፓርቲው ለውድድር በቀረበባቸው ቦታዎች 13 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 73 የክልል እና የከተማ ምክር ቤት ወንበሮችን በድምሩ 86 መቀመጫዎችን በማግኘት በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚው ተፎካካሪ ፓርቲ ሆኖ ማጠናቀቁንም ገልጿል።
ይህንን ተጨባጭ ስኬት ላስመዘገቡ የፓርቲው ዕጩዎች፣ አባላት፣ ደጋፊዎች እና በሂደቱ በቅንነት ለተሳተፉ አካላት ሁሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ፓርቲው ጥንካሬዎቹን በማስቀጠልና ክፍተቶቹን በስትራቴጂ በመሙላት እውነተኛ ተፎካካሪ ሆኖ መሥራት እንደሚጀምርም አመልክቷል።
በቀጣይም በብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ከሁሉም የኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በትብብር እንደሚንቀሳቀስ የገለጸው ፓርቲው፤ ልዩነቶችን በጨዋነት በማንጸባረቅ የጀመረውን ዘመናዊ የፖለቲካ ባህል ለማሳደግና ለተጨማሪ ስኬት ለመዘጋጀት ቃል ገብቷል።
በመጨረሻም ገዢ ሆኖ እንዲቀጥል ለተመረጠው ብልጽግና ፓርቲ እንዲሁም በውድድሩ ተሳትፋችሁ የሕዝብ ውክልናን ላሳካችሁ ተፎካካሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብሏል።

