Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በምርጫ ሒደቱ ሴቶች በነፃነት እንዲመርጡ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል – የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማሕበር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሴቶች በነፃነት እንዲመርጡ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል አለ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማሕበር።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ማሳወቂያ መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡

የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ሕብረት አባሆይ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ማሕበሩ በ9 ክልሎች፣ 18 ዞኖችና በ6 ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በሚገኙ 136 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫ ሒደቱን በቅርበት ተከታትሏል።

በተደረገው ምልከታም 97 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆኑ የምርጫ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ ሆነው መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

ስኬቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የፀጥታ አካላት፣ መራጮች እና ተጎጂን ማዕከል ያደረጉ የመከላከያ ስልቶች በተቀናጀ ሁኔታ በመተግበራቸው የተገኘ ውጤታማ ጥረት ማሳያ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም 92 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ለተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ መስጠታቸውን አመልክተዋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫው ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የወሰደው ሁሉን አቀፍ ቅድመ ዝግጅት የሚደነቅ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ቦርዱ ተጎጂን ማዕከል ያደረጉ አሠራሮችና መመሪያዎችን በማዘጋጀትና በመተግበር ሴቶች በዴሞክራሲያዊ ሒደቱ በነፃነት እንዲሳተፉ አዲስ በጎ ተሞክሮ መፍጠሩን አመልክተዋል።

ከዓለም አቀፍ አጋር ተቋማት ጋር ለምርጫ ታዛቢዎች ስልጠና በመስጠት በጾታ ላይ የተመሰረቱ ተግዳሮቶችን የመለየትና የመመዝገብ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው÷ ይህም የሲቪል ማሕበረሰብ የምርጫ ታዛቢነት ወሳኝ ሚና እንዳለው የሚያሳይ ጥሩ ጅምር መሆኑን አስረድተዋል።

በቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የተዘረጋውን ተጎጂን ማዕከል ያደረገ የአሠራር ሥርዓት ማጠናከርና የስልጠና መርሐ ግብሮችን ማስፋፋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ማሕበሩ በቀጣይ ሴቶች የመምረጥ፣ የመመረጥና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ከስጋት ነጻ በሆነ ሁኔታ የሚጠቀሙበትን ምህዳር ለመፍጠር በቁርጠኝነት መሥራቱን እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version