አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሕብረተሰቡን ችግሮች ከመፍታት ባለፈ የመደጋገፍ ማህበራዊ እሴቶችን እያሳደገ ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን።
ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት÷ በክልሉ የበጎ ፍቃድ ተግባራት በየጊዜው እያደጉ በመምጣታቸው የሕዝቡን የልማትና ማህበራዊ አገልግሎቶች ለማሳለጥ እያገዙ ናቸው።
ተግባሩ የመንግሥትን በጀት ከመቆጠቡ ባለፈ የሕብረተሰቡን የአብሮነትና መረዳዳት ማሕበራዊ እሴት እያጠናከረ መሆኑን አስረድተዋል።
ለአብነትም በክልሉ በበጎ ፈቃድ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የቤት ግንባታ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ ያሳዩ እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ተግባሩ የመንግሥትን ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች ከማሳደጉ ባለፈ አቅም ለሌላቸው የማሕበረሰብ ክፍሎች አለኝታ መሆን እንደቻለ ተናግረዋል።
በቀጣይም ወጣቶችና የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ለማስፋት ወደ ሥራ መገባቱን ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
በዘንድሮው የክረምት ወራት ከ984 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተጠቁሟል፡፡

