Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዝዋይ ሐይቅን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም…

ዌትላንድስ ኢንተርናሽናል እና ሼር ኢትዮጵያ የዝዋይ ሐይቅን መልሶ በማቋቋም ወደ ነበረበት ለመመለሰ የሚያስችል ንቅናቄ ይፋ አድርገዋል፡፡

ንቅናቄው የአካባቢውን መልክዓ ምድር እና የዝዋይ ሐይቅ የደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ የሐይቁ አካባቢ ነዋሪዎችን የአኗኗር ዘዬ ለማሻሻል ጉልህ ሚና አለው፡፡

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ ኤምባሲ ድጋፍ የሚተገበረው የዝዋይ መልሶ ግንባታ ንቅናቄ በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን ተመላክቷል፡፡

መርሐ ግብሩ ለሐይቁ መመናመን ምክንያት የሆኑ ተግዳሮቶች ማለትም የመሬት መሸርሸር፣ ደለል እና የአፈር ጥበቃ ውስንነት እና ሌሎች ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡

ዌትላንድስ ኢንተርናሽናልን ንቅናቄውን በዝዋይ አካባቢ ዓለም አቀፍ እውቀትና ልምድ ካለው የሮዝ አምራች ኩባንያ ሼር ኢትዮጵያ የቴክኒክና የግብርና ክህሎትን እንዲሁም ሃብቶችን በማጣመር እንደሚተገብረው አስታውቋል፡፡

ንቅናቄው በዝዋይ ሐይቅ እና አካባቢው ለተከሰተው ችግር መንስኤዎችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣቻዎችን ለማመላከት እንደሚሰራ ነው የተገለጸው፡፡

በዝዋይ ሐይቅ አካባቢ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ለችግሩ ነባራዊ ሁኔታው ያገናዘበ እና ቅቡልነት ያለው መፍትሄ ለማፈላለግ እንደሚሰራ ተጠቅሷል፡፡

የፕግራሙ አስተባባሪ  አቶ ስሜነህ ሽፈራው እንዳሉት ÷ በዝዋይ ሐይቅ የተጋረጠውን አደጋ መቀልበስ የሚቻለው ሁሉም በለድርሻ አካላት ማህበረሰቡን ጨምሮ በትብብረ ሲሰሩ ብቻ ነው፡፡

ስለሆነም በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት፣ መንግሥታዊ፣ የግልና አጋር ድርጅቶች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ ለፕሮግራሙ ስኬታማነት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የንቅናቄ ሥራው በዋናነት በሶስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ እንደሚያተኩርም ነው አስተባባሪው አጽንኦት የሰጡት፡፡

እነዚህም የተሻሉ አሰራሮችን በመዘርጋት ከአርሶ አደሮች ጋር በመተባበር ይበልጥ ዘላቂ የውሃ አጠቃቀምን ማጠናከር፣ የአፈር መሸርሸርንና የደለል መሙላትን ለመቀነስ በተፈጥሮ ላይ መስራትና የውሃ መጠንና ጥራትን ለማሳደግ ውጤታማ ውሳኔ ማሳለፍ የሚሉ ናቸው፡፡

Exit mobile version