አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን በማፅዳት አካባቢያቸውን ከጎርፍ አደጋ እንዲጠብቁ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ፡፡
በመዲናዋ በዘንድሮው የክረምት ወራት የሚተገበር የጎርፍ መከላከልና የአደጋ ዝግጁነት ንቅናቄ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ንቅናቄው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተደጋጋሚ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆነ አካባቢ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
አቃቂ ቃሊቲ በተፈጥሯዊ አቀማመጡ የአዲስ አበባ የታችኛው ክፍል በመሆኑ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ ሲያስተናግድ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ለዚህ አካባቢ ቅድሚያ በመስጠት በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች ላይ ወንዞች ተፈጥሯዊ ፍሰታቸውን ጠብቀው እንዲፈሱ የተለያዩ ግንባታዎችና የፍሳሽ መስመሮችን የማፅዳት ንቅናቄን አስቀጥለናል ብለዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በዚህ የአደጋ መከላከል የቅድመ ዝግጁነት ስራ ላይ እንዲሳተፉ ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ቆሻሻን ወደ ፍሳሽ መውረጃ ባለመጣልና በአግባቡ በማስወገድ አካባቢያችሁን ከጎርፍ አደጋ እንድትጠብቁ አሳስባለሁ ነው ያሉት።

