አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋራ ችግሮችን በትብብር ለመፍታት በጥናት ላይ የተመሰረቱ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማቅረብ ይገባል አሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት “የመንግሥታት ግንኙነት በኢትዮጵያ፡ መልካም ዕድሎች፣ ፈተናዎችና መፍትሔዎች” በሚል መሪ ሀሳብ ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የጋራ ችግሮችን በትብብር ለመፍታት ተቋማዊ የምክክርና የትብብር ፎረሞችን ማጠናከር ይገባል፡፡
የመንግሥታት ግንኙነት ዋና ዓላማ የሕገመንግሥቱን ድንጋጌዎች ማስጠበቅ፣ የሕዝቦችን ግንኙነትና ትስስር ማጠናከርና ሀገራዊና ክልላዊ ዕቅዶች ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲፈጸሙ ማድረግ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም መንግስታት በአጋርነትና በትብብር ላይ የተመሠረተ የአመራር መርህ በመከተል በጋራ የሚመሩበትንና የሚመክሩበትን ሥርዓት መገንባት ይገባል ነው ያሉት፡፡
የጋራ ችግሮችን በትብብር ለመፍታት ተቋማዊ የምክክርና የትብብር ፎረሞችን ማጠናከር እንዲሁም በጥናት ላይ የተመሰረቱ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማቅረብ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ይህም የፌዴራል ሥርዓቱን ውጤታማ በማድረግ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው እንዲሁም ዴሞክራሲ የሰፈነበት አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት ለተቀመጠው ሀገራዊ ግብ መሳካት መሠረት የሚጥል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

