Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ ትገነባለች…

ሀገር የአንድ ወቅት ስራ ወይም የአንድ ወገን ስኬት ውጤት ብቻ አይደለችም፡፡

ሀገር የምትገነባው በቅብብሎሽ ነው፡፡

እያንዳንዱ ትውልድ የተረከበውን አደራ ተወጥቶ፣ የራሱን አሻራ አሳርፎ ለሚቀጥለው ትውልድ ያስተላልፋል፡፡

የኢትዮጵያን ታሪክ ስንመረምር፣ ዛሬ ያለንባት ሀገር የብዙ ትውልዶች የደምና የላብ መስዋዕትነት ውጤት መሆኗን እንረዳለን።

የቀድሞው ትውልድ የሀገርን ዳር ድንበር እና ነፃነት አስከብሮ አቆይቶልናል፡፡

የዓድዋን ድል ጨምሮ በርካታ ታሪካዊ ተጋድሎዎችን ያደረጉት አባቶቻችን እና እናቶቻችን፤ ዋነኛ ተልእኳቸው ሀገርን ከባዕድ ወራሪ ጠብቆ ማቆየት ነበር።

እነሱ ለአንድነቷና ለነፃነቷ መስዋዕትነትን ከፍለው ነፃ ሀገር አስረክበውናል።

የ1960ዎቹ እና 70ዎቹ ትውልድ ደግሞ የኢትዮጵያን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅር ለማሻሻል፣ የትምህርት እድልን ለማስፋፋት እና የእኩልነት ጥያቄዎችን ለመመለስ ከፍተኛ ምሁራዊ ተጋድሎ አድርጓል።

ለተቋማት ግንባታ እና የዘመናዊነት መሠረትንም ለመጣል የራሱን አሻራ አኑሯል፡፡

እኛ የዛሬዎቹ ትውልዶች እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሉ እና ማህበረሰቡን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየሰራን ነው፡፡

የባህር በር ባለቤትነትን ለማሳካት እና የኢኮኖሚ ነፃነትን ለማረጋገጥ እረፍት የሚያስፈልገንም አይመስልም፡፡ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በፈጠራ ስራዎች ሀገርን ከዘመኑ ጋር ለማስተሳሰርም ደፋ ቀና እያልን ነው፡፡

ከዚህም በላይ ሀገሪቷ የገጠሟትን ስብራቶች ጠግነን የማለፍ ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን።

አዲሱ ትውልድ፣ ያለፉት ትውልዶች የሰሯቸውን ታላላቅ ስራዎች ማክበር፣ ስህተቶቻቸውን የልዩነቶች ምንጭ ከማድረግ ለዛሬው ጉዞ መማሪያ ማድረግ አለበት። ታሪክን ሙሉ በሙሉ የማፍረስ አባዜ የሀገርን መሰረት ያናጋል።

እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን ዘመን ቴክኖሎጂ፣ እውቀትና ጥበብ ተጠቅሞ በሀገሪቱ ላይ አዲስ እሴት መጨመር ይኖርበታል።

በትውልዶች መካከል የሚኖረው የስልጣን እና የኃላፊነት ሽግግር በግጭት ሳይሆን በውይይት፣ በስርዓት እና በሰላማዊ መንገድ እንዲሆን መስራት አለብን፡፡

ሰላማዊ ሽግግርን ማጠናከር ለሀገር ሉዓላዊነት አስፈላጊ ነው፡፡

ይህ እንዲሳካም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የጀመራቸውን ሥራዎች እንዲያጠናቅቅ የበኩላችንን መወጣት አለብን፡፡

ሀገር በግለሰቦች ፍላጎት ሳይሆን ትውልድ ተሻጋሪ በሆኑ ጠንካራ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የፍትህ ተቋማት ላይ መገንባት አለባት። ሀገር እንድትቀጥል ተቋማዊ ቀጣይነትን መገንባት ወሳኝ ነውና፡፡

ኢትዮጵያ ገና ተገንብታ ያላለቀች ታላቅ ህንፃ ናት።

እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን ጡብ ያስቀምጣል እንጂ ህንፃውን ብቻውን አይጨርሰውም።

የአሁኑ ትውልድ ዛሬ የሚሰራቸው ስራዎች በሙሉ ነገ ለሚመጣው ትውልድ የሚተላለፉ መሆናቸውን ልብ ማለት አለበት፡፡

ጥላቻን፣ መከፋፈልን እና ጦርነትን የምናወርስ ከሆነ የቅብብሎሹ ሰንሰለት ይቋረጣል፤ ፍቅርን፣ እውቀትን፣ ተቋማትን እና ልማትን ካስተላለፍን ግን የኢትዮጵያ ህልውና ለዘላለም ይኖራል።

ሀገር የምትጸናው ትውልድ በትውልድ ላይ ሲደመር ብቻ ነው፡፡

ኑ፤ ሀገር እንገንባ!

Exit mobile version