Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዳታ፤ የዲጂታል ስርዓት የደም ስር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዳታ በዲጂታል ዓለም ውስጥ መረጃን፣ ውሳኔን እና ፈጠራን የሚያንቀሳቅስ ዋና ኃይል ሆኗል።

ዛሬ ትላልቅ ኩባንያዎች የደንበኞቻቸውን ፍላጎት ለመረዳት፣ መንግሥታት ውጤታማ ፖሊሲዎችን ለማዘጋጀት፣ እንዲሁም ሳይንቲስቶች የወደፊቱን ችግሮች ለመተንበይ በዳታ ላይ ይመሰረታሉ።

ዲጂታል ስርዓት መረጃን በኤሌክትሮኒክ መንገድ የሚሰበስብ፣ የሚያከማች፣ የሚያቀናብር እና የሚያስተላልፍ የቴክኖሎጂ አውታር ነው።

የባንክ ስርዓቶች፣ የኢ-ኮሜርስ መድረኮች፣ የጤና መረጃ ስርዓቶች፣ የትምህርት አስተዳደር ፕላትፎርሞች እና ሌሎችም የመንግሥት አገልግሎቶች የዲጂታል ስርዓት ምሳሌዎች ይሆናሉ።

እነዚህ ስርዓቶች በትክክል እንዲሰሩ ደግሞ ዳታ ያስፈልጋቸዋል። ዳታ ከሌለ ስርዓቱ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። የተሳሳተ ወይም ያልተሟላ ዳታም ትክክለኛ ውጤት አያስገኝም።

ዳታ የዲጂታል ስርዓት የደም ስር ነው የሚባለውም ከዚህ አንጻር ሲሆን፥ በሰውነት ውስጥ ደም ኦክስጅንና ምግብ ወደ አካላት እንደሚያደርስ ዳታም መረጃን ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ በማስተላለፍ ስርዓቱ በቅልጥፍና እንዲሰራ ያግዛል።

የዳታ ደም ስርነት ከሚታይባቸው ጉዳዮች መካከል፥ ውሳኔ ሰጭነት፣ ቅልጥፍና ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሁም ፈጠራና እድገት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

ዳታ አስፈላጊውን ጠቀሜታ እንዲሰጥ በትክክል መሰብሰብ፣ ጥራቱን በተከታታይ መፈተሽ፣ ከሳይበር ጥቃት ለመከላከል ጠንካራ የደህንነት ስርዓቶች መፍጠር እና የግል መረጃ ምስጢራዊነት መጠበቅ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ በዘርፉ እያደረገች ባለው ፈጣን ሽግግር የተነሳ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚው በፍጥነት እየተሸጋገረች ትገኛለች።

በመንግሥት አገልግሎቶች፣ በባንክ ዘርፍ፣ በትምህርትና በጤና ዘርፎች ዲጂታል ለውጦች በመስፋፋት ላይ ናቸው።

ይህ ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው የተደራጀ የዳታ አስተዳደር፣ የዳታ ጥራት እና የዳታ ደህንነት በትኩረት ሊሰሩባቸው ይገባል።

ዲጂታል ስርዓቶች የዘመናዊ ኢኮኖሚና ማህበረሰብ መሠረት ከመሆናቸው አንጸር በእነዚህ ስርዓቶች ውስጥ ዳታ የሚጫወተው ሚና ደም በሰውነት ውስጥ ያለውን ሚና ያህል ወሳኝ ነው።

ትክክለኛ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና በአግባቡ የሚተዳደር ዳታ ካለ ዲጂታል ስርዓቶች ውጤታማ፣ ተዓማኒ እና ዘላቂ ሊሆኑ ይችላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት እና የፖሊሲ ነጻነትን ለማረጋገጥ የዳታ ሉዓላዊነት ቁልፍ እና መሰረታዊ ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያን የዳታ የመሰብሰብ፣ የማደራጀትና የመተንተን አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገሩ የዘርፉ ሙያተኞች ባለፉት ዓመታት ተፈጥረዋል።

ሉዓላዊነት የሀገርን ድንበርና አካላዊ አቅምን መከላከል ብቻ ሳይሆን የዳታ፣ የምግብ እና የፖሊሲ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥም ጭምር በመሆኑ የዳታ አስተዳደር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ይገኛል።

በአመለወርቅ ደምሰው

Exit mobile version