አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ጨዋታን መሰረት ያደረገ የሕጻናት መማር ማስተማር ሒደት ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ትምህር ቢሮ፡፡
ራይት ቱ ፕሌይ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ዓለም አቀፍ የጨዋታ ቀንን “በጨዋታ የታገዘ የሕጻናት ትምህርትን ማጠናከር” በሚል መሪ ሃሳብ አክብሯል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ የክልሉ ሴቶችና ሕጻናት እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ አመራሮች እንዲሁም ርዕሳነ መምህራን፣ መምህራን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
በኦሮሚያ ት/ቢሮ የ1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ዳይሬክተር አቶ ሸምሰዲን ኢብራሂም በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ደረጃውን የጠበቀ የሕጻናት ትምህርትን በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
መንግሥት ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ትኩረት መስጠቱን ጠቁመው ÷ በራይት ቱ ፕሌይ ለሚተገብረው ጨዋታን መሰረት ያደረገ የሕጻናት ትምህርት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የራይት ቱ ፕሌይ ፕሮጀክት ማኔጀር ሙሉጌታ ጋቢሳ በበኩላቸው ÷ የፕሮጀክቱ ዋና አላማ ጨዋታን መሰረት ያደረገ የሕጻናት ትምህርት በመስጠት የመማር ማስተማር ሒደቱን ውጤታማ ማድረግ ነው፡፡
ለአምስት ዓመታት የሚከናወነው ፕሮጀክቱ አሁን ላይ በቢሾፍቱ ከተማ እና በሉሜ ወረዳ እየተተገበረ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች የማንበብ ክህሎታቸውን ለማዳበር ጨዋታን መሰረት ያደረገ ትምህርት እንዲሰጥ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም የመምህራንንና የትምህርት ባለሙያዎችን አቅም በሥልጠና ማሳደግ እንዲሁም የተለያዩ የትምህርት ግብዓቶችንና የስፖርት ቁሳቁሶችን ማሟላት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም ለሕጻናት የሚመጥን ይዘት ያላቸውና ሳቢ የሆኑ ታሪኮችን የያዙ 75 ሺህ በላይ መጽሐፍትን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል፡፡
ጨዋታ ለሕጻናት ትምህርት ትልቅ አቅም ነው፤ ጨዋታን በመጠቀም የንብባ ክህሎታቸውን ማሻሻል፣ ሥነ ልቦናቸውን ማጠናከር እንዲሁም በአካል፣ በጤና እና በአእምሮ የበለጸጉ ሕጻናትን ማፍራት እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡
ስለሆነም ጨዋታን መሰረት ያደረገ የሕጻናት ትምህርትን ለማጠናከር ባለድረሻ አካላት ከራይት ቱ ፕሌይ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡

