Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አረንጓዴ ዐሻራ ለሥርዓተ ምህዳር ጥበቃና ለዘላቂ ልማት ጉዞ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት እየተተገበረ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሀገሪቱን ከተጋረጠባት የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ መራቆት አደጋ ለመታደግ የተጀመረ ሀገራዊ ግዙፍ ኢኒሼቲቭ ነው።
መርሐ ግብሩ ወደ ተግባር ከገባበት 2011 ዓ.ም ጀምሮ አንስቶ በርካታ ትሩፋቶችን እያስገኘ ሲሆን፤ በተለይም የሥርዓተ-ምህዳር ጥበቃን በማጠናከር እና ተመናምኖ የነበረውን የብዝሃ ሕይወት ሀብት በመጠበቅ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ቀደም ሲል የተራቆቱ እና ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢያዊ ስርዓተ ምህዳሮች እንዲታደሱ እና እንዲለመልሙ አድርጓል። ከዚህም ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል፣ የመሬት እና የውሃ ሀብት ጥበቃ እና በረሃማነትን በመከላከል ረገድ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
ባለፉት ዓመታት የተተከሉ የዛፍ ችግኞች እየተመናመነ የነበረውን የኢትዮጵያን የደን ሀብት የታደገ ሲሆን፤ የደን ሽፋኑ ከ23 ነጥብ 6 በላይ ሊደርስ ችሏል።
ይህም ወደ ከባቢ አየር ይለቀቅ የነበረውን ግዙፍ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋዝ በመምጠጥና ንጹህ አየርን በመፍጠር ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መዛባት መፍትሄ ሆኗል።
በደን መራቆት የተነሳ ያጋጥም የነበረውን የመሬት መንሸራተት አደጋ በመከላከል፣ የጎርፍ አደጋን በመቀነስ እና የውሃ ሀብትን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
በድርቅና በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት የሚችልን በረሃማነት በመግታት ረገድ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ያመጣው ውጤት በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ከዚህም ባለፈ የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር ውሃ ሃብትን በማጎልበት የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር አግዟል።
በነዚህም ሁለንተናዊ አበረታች ውጤቶች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕውቅና እንድታገኝ አስችሏታል።
መርሐ ግብሩ ለአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ማህበራዊ ደህንነት ከፍተኛ ድጋፍ እየሰጠ ሲሆን፤ ለምግብ ዋስትና እና ምርታማነት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለአርሶ አደሮች ገቢ ማደግ ላይ የበኩሉን ድርሻው እየጨመረ መጥቷል።
የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እና በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት እያገዘ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፤ በችግኝ በማፍላት፣ በመትከል እና በመንከባከብ ሂደቶች ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
የደን ሽፋን ማደግ፣ የደን መጨፍጨፍ መቀነስ እና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተተክለው ለፍሬ መብቃታቸው ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እየሆኑ ነው።
ማህበረሰቡ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ጠቀሜታ በሚገባ በመረዳቱና በንቃት በመሳተፉ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር የማስረከብ ርዕይ ተስፋ ሰጪ ሆኗል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የዛሬዋን ኢትዮጵያ አረንጓዴ ለብሳ ከማየት ባለፈ፤ የነገውን ትውልድ ህልውና የሚጠብቅ የዕድገት ምሰሶ ነው።
በመሆኑም መላው ሕዝብ ለሀገርና ለትውልድ ሲል መርሐ ግብሩን በባለቤትነት በመምራትና በመንከባከብ ዘላቂነቱን ማረጋገጥ ይገባል።
በአቤል ነዋይ
Exit mobile version