Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በምክክር ኢትዮጵያን እናፅና…

ምክክር ውስብስብ ችግሮችን በሰላማዊ፣ በሥልጡን እና ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት ያስችላል፡፡
ግጭቶችን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ በመመካከር ለመፍታት መሥራት ሁለንተናዊ ጥቅሞች አሉት፡፡
መመካከር የሰው ልጅ ካካበታቸው እጅግ ሥልጡን፣ ሰላማዊና ዘላቂ የችግር መፍቻና የዕድገት መሣሪያዎች መካከል ቀዳሚው ነው።
ግለሰቦች፣ ማኅበረሰቦች ወይም ሀገራት የሚያጋጥሟቸውን ውስብስብ የሐሳብ፣ የጥቅምና የታሪክ ልዩነቶች በኃይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ሲመክሩ ዘላቂ መፍትሄ ያበጃሉ፡፡
ምክክር የአንድ ወገን ተሸናፊነት ወይም የሌላኛው ወገን አሸናፊነት የሚረጋገጥበት ሳይሆን፣ ሁለቱም ወገኖች አሸናፊ የሚሆኑበት የሥልጣኔ አውድ ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ካጋጠሟት ታሪካዊና መዋቅራዊ ችግሮች ወጥታ ጠንካራ የሀገረ-መንግሥት መሠረት መጣል የምትችለው፣ ዜጎቿ ልዩነቶቻቸውን በጦር ሜዳ ሳይሆን በምክክር አደባባዮች ላይ ማስተናገድ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት የቆዩ መዋቅራዊና ፖለቲካዊ ቅራኔዎች አሉ፡፡ እነዚህን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና የማይናወጥ ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ለመገንባት ምክክር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
በሀገራዊ ምልክቶች (ሰንደቅ ዓላማ)፣ በሕገ-መንግሥት መዋቅር፣ በማንነት ጥያቄዎች እና በታሪክ ትረካዎች ላይ በፖለቲካ ልሂቃኑና በማኅበረሰቡ መካከል መሠረታዊ ልዩነቶች አሉ፡፡
ምክክር እነዚህን ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ በማንሳት የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ወሳኝ ነው፡፡
ልዩነቶችን በኃይልና በጦርነት ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ለሀገሪቱ ሰብአዊ፣ ቁሳዊና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስን ብቻ ነው ያተረፉት፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሰላማዊ ውይይት፣ የድርድር እና የመደማመጥ ባህልን ለመገንባትና የጠብመንጃ ፖለቲካን ለማክሰም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
ቀደም ሲል የሚደረጉ የፖለቲካ ስምምነቶች በታጣቂ ኃይሎችና በገዥው ፓርቲ መካከል ብቻ የሚደረጉ በመሆናቸው ዘላቂ ሰላምን ማምጣት አልቻሉም።
ነገር ግን ሰፊ መሠረት ያለውን የቆዩ መዋቅራዊና ፖለቲካዊ ልዩነቶችን አካታች፣ ገለልተኛና ግልጽ በሆነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት በመፍታት፣ የጋራ መግባባትን ለመፍጠርና የማይናወጥ ጠንካራ የሀገረ-መንግሥት መሠረት ለመጣል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚሠራቸው ስራዎች ወሳኝ ናቸው፡፡
በዚህ የምክክር ሂደት በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 1,234 ወረዳዎች ወይም ከ93% በላይ የሀገሪቱን አካባቢዎች ባካተተ መንገድ አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ ተሰርቷል፡፡
የምክክር ሂደቱና አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራው ከእያንዳንዱ ወረዳ የተወጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን (የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ መምህራን፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና የሲቪል ማኅበራት) ያካተተ ነው፡፡ ይህም ሕዝባዊ መሠረት ያለው ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ለመገንባት ይጠቅማል፡፡
በሥራው ለዋናው ጉባኤ የሚቀርቡ መሰረታዊ ሀገራዊ አጀንዳዎችን ከተለያዩ ወገኖች በገለልተኝነት የመሰብሰብ ሥራ ተጠናቋል፡፡ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በሐረሪ፣ በጋምቤላ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደቶች በስኬት ተጠናቀው ተደራጅተዋል።
ከተሰበሰቡት ሐሳቦች መካከል አብዛኛዎቹ የፍትሕ፣ የማንነት ጥያቄዎች፣ የአስተዳደር ወሰን፣ ሕገ-መንግሥት እና ሀገራዊ ምልክቶች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ኮሚሽኑ ለይቷል። ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች የጽሑፍና የዲጂታል አጀንዳ ምክረ-ሐሳቦችን ተቀብሏል።
በትግራይ ክልል በነበረው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን እዚያው ማከናወን ባይቻልም፣ ኮሚሽኑ ሂደቱ አካታች እንዲሆን በትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላትና በአዲስ አበባ በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች መካከል የመጀመሪያ ዙር የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክን በአዲስ አበባ በአማራጭነት በስኬት አከናውኗል።
የኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በርካታ መዋቅራዊና ስትራቴጂካዊ ሥራዎችን አከናውኗል። ታሪካዊውን ሀገር አቀፍ የውይይት ምዕራፍ ለመጀመርም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት ወደ ዋናውና ታሪካዊው የሀገር አቀፍ ምክክር ጉባኤ ለመግባት የሎጂስቲክስና የዕውቀት ዝግጅቶችን አጠናቋል፡፡
ታሪካዊው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ሳምንታት በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል። ለዚህ ትልቅ ሀገራዊ ጉባኤ ከመላ ሀገሪቱ የተወጣጡ 4,000 ገደማ ተወካዮች በአንድ አዳራሽ እንዲመክሩ ዝግጅቱ ተጠናቋል።
ምክክሩ ሀገሪቱ ከገጠሟት ውስብስብ የፖለቲካ ውጥረትና አለመግባባቶች ወጥታ ዘላቂ ሰላም የምታረጋግጥበት ብቸኛና ቁልፍ ታሪካዊ ዕድል ይሆናል፡፡
ስለሆነም መመካከርን እንደ ባህል ማሳደግ፣ እርስ በርስ ለመደማመጥ ዝግጁ መሆን እና የውይይት መድረኮችን በቅንነት መደገፍ የእያንዳንዱ ዜጋ የህልውና እና የሰላም አደራ ነው።
ኑ፤ በምክክር ኢትዮጵያን እናፅና፤ ጠንካራ ሀገረመንግሥት እንገንባ!
Exit mobile version