Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የገጠር ሽግግር ለኢትዮጵያ ማከናወን…

በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ሁለንተናዊ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡
ወደ ትግበራ የገባው የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የገጠር ኢኮኖሚን ሙሉ በሙሉ ለማዘመንና ሁለንተናዊ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት አልሟል፡፡
የገጠር ሽግግር ዋናው ዓላማ አርሶ አደሩ ለራስ ፍጆታ ብቻ ከሚያመርትበት ባህላዊ አሰራር ወጥቶ ለገበያ የሚተርፍ ምርት እንዲያመርትና ተረጂነትን በዘላቂነት ማስወገድ ነው።
ከስትራቴጂው ትኩረቶች መሀከል አንደኛው የተቀናጀ የገጠር መሰረተ-ልማቶችን ማስፋትና አገልግሎቶችን ማዳረስ ነው፡፡
በግብርናውና በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር ደግሞ ሌላኛው ወሳኙ ጉዳይ ተደርጎ እየተሰራበት ይገኛል፡፡
ለግብርና እድገት ድጋፍ የሚሰጡና የከተማ-ገጠር ትስስርን የሚያሳልጡ ከእርሻ ውጭ ያሉ (Non-farm) የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ማበረታታት እና ጠንካራ ተቋማትን መገንባትም እንዲሁ ወሳኝ ጉዳይ ይሆናል፡፡
አሳታፊ የፋይናንስ ስርዓትን መዘርጋትና የገጠሩን ማህበረሰብ ከኢኮኖሚው ተጠቃሚ በማድረግ የኑሮ ሁኔታውን ማሻሻል ሌላኛው የሽግግሩ የትኩረት መስክ ነው።
ይህንን ለማሳካት ኢትዮጵያ ጉዞ ጀምራለች፡፡ ሽግግሩን ለማፋጠን በርካታ የእርሻ ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነፃ በማስገባትና በሀገር ውስጥ በመገጣጠም ለአርሶ አደሩ እያቀረበች ትገኛለች፡፡
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ለገጠርም ሆነ ለመዋቅራዊ ሽግግር መሠረት ነው፡፡
ተገቢው ሽግግር የሚመጣው አርሶ አደሩ ለራስ ፍጆታ ብቻ ከሚያመርትበት የአሰራር ዘይቤ ወጥቶ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ማምረት ሲችል ነው፡፡
ይህም ለገጠር መሠረተ ልማት መስፋፋት ማለትም ለኤሌክትሪክ፣ ለመስኖ፣ ለመጋዘን፣ ለምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች፣ ለመንገድና ለዲጂታል ትስስር መጠናከር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
የገጠር ትራንስፎርሜሽን ምሰሶዎች ገበያ ተኮር ግብርና፣ የገጠር ፋይናንስ፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ ማህበራዊ ልማትና ጠንካራ ተቋማት ግንባታ እንዲሁም ሰላማዊ አብሮነት ናቸው፡፡
ሽግግሩ ከበሬ ትከሻ እርሻ ወደ ዘመናዊ ግብርና ነው፡፡ ትራክተር፣ ኮምባይነር እና የውሃ መሳቢያ ፓምፖችን ወደ መጠቀም፡፡
ለዚህ እንዲመች ደግሞ አርሶ አደሮች መሬታቸውን አስተናብረው ተመሳሳይ ሰብሎችን በኩታ ገጠም በማልማት ምርታማነታቸውን ማሳደግ ጀምረዋል፡፡
ለምሳሌ፣ በበጋና በክረምት የሚመረተው የስንዴ ልማት ሀገሪቱ በምግብ ራሷን እንድትችልና ወደ ውጭ እንድትልክ መንገድ ከፍቷል።
አርሶ አደሮች እንደ ስንዴ፣ አቮካዶ፣ ፓፓያ እና ሙዝ ያሉ ምርቶችን በጋራ በማልማት ከፍተኛ የገበያ ፍላጎትን ለማሟላትና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ፣ የመስኖ፣ የመጋዘንና የምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ምርቱ ባለበት እዚያው በገጠር በማሟላት የዲጂታል ትስስርን በማረጋገጥ ሀገራዊ ለውጡን ለማሳካት እየሰራች ትገኛለች፡፡
ለአርሶ አደሩ የብድር እና የቁጠባ አቅርቦቶችን በማመቻቸት የኢኮኖሚ አቅሙን መገንባት ላይም ናት።
ኢትዮጵያ አቅዳ እየተገበረች ያለችው የገጠር ሽግግር በውጭ እርዳታ ላይ ያለንን ጥገኝነት በማስቀረት፣ በራስ መተማመን ላይ የተገነባና የማይበገር ኢኮኖሚ ለመፍጠር ይረዳል፡፡
ኑ፤ ሀገር እንሥራ!
Exit mobile version