Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ታከናውናለች… የኮሪደር ልማት ለዘመናዊነትና ለሕዝብ ተጠቃሚነት…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የጀመረቻቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የከተሞችን ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ገጽታ በከፍተኛ ፍጥነት እየቀየሩ ይገኛሉ።

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል የሆነው እና በመደመር እሳቤ የታገዘው የኮሪደር ልማት ሥራም ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለኢንቨስትመንት ተመራጭና ከዓለም አቀፍ የከተሞች ዕድገት ደረጃ ጋር ተወዳዳሪ የማድረግ ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ ስኬት ማሳያ ነው።

ይህ ዘመናዊ የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማን ባልተቀናጀ መልኩ ከመገንባት ወጥቶ ሁሉንም የመሠረተ ልማት አውታሮች ማለትም መንገዶችን፣ የእግር ጉዞ መንገዶችን፣ የአረንጓዴ ሥፍራዎችንና የፍሳሽ ማስወገጃዎችን በተቀናጀ እና ተመጋጋቢ በሆነ መልኩ ማልማትን መሠረት ያደረገ ነው።

ፕሮጀክቱ ከተሞች ወደ ዘመናዊነት፣ ውበትና ሥልጣኔ እንዲሸጋገሩ ያደረገ ሲሆን÷ በተለይም በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ ክልላዊ ከተሞች በተከናወኑት የኮሪደር ልማት ሥራዎች አስደናቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍኑ ዘመናዊ የውስጥ ለውስጥና የዋና ዋና መንገዶች ግንባታዎች ተከናውነዋል፡፡ ሰፋፊና ምቹ የእግር ጉዞ መንገዶች እንዲሁም የብስክሌት መስመሮች መገንባታቸው የከተማ ትራፊክ እንቅስቃሴ መጨናነቅን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ አስችሏል።

እንዲሁም የዚህ ፕሮጀክት ሌላኛው ደማቅ ስኬት በሆነው የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት በተሰሩ አረንጓዴያማ የመንገድ ዳርቻ፣ የሕዝብ መዝናኛ መናፈሻዎች፣ ዘመናዊ የመብራትና ሌሎች የማስዋብ ሥራዎች የከተሞችን የሌሊትና የቀን ገጽታ ሙሉ በሙሉ ቀይረውታል።

ይህ ስኬት ከተሞቻችንን ለቱሪስትና ለውጭ ኢንቨስትመንት ሳቢ ከማድረጉም በላይ ነዋሪዎች የአዕምሮ ዕረፍትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸውን ንፁህ የጋራ ስፍራዎች ፈጥሯል።

የኮሪደር ልማት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በማቀላጠፍና የንግድ ሥርዓቱን በማዘመን ረገድ ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተ ሲሆን ÷ ለብዙ ሺህ ዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን አበርክቷል።

ከዚህም በላይ በልማቱ ምክንያት የተነሱ ዜጎች የተሻለ ደረጃ ባላቸው ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶችና የንግድ ቦታዎች እንዲተኩ መደረጉ፣ የሪፎርሙን “ዜጋ ተኮር” እና ፍትሐዊ የልማት መርህ የተከተለ መሆኑን በተጨባጭ ያሳየ ነው።

በአጠቃላይ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተማ ዘመናዊነት ደረጃን ከማሻሻልና ውበትን ከመፍጠር ባለፈ የዜጎችን የኑሮ ጥራትና ሥልጣኔ ከፍ ያደረጉ ታሪካዊ ርምጃዎች ናቸው።

በኢትዮጵያ የሚታይና የሚዳሰስ ለውጥ ማምጣት ያስቻለው የኮሪደር ልማት ኢትዮጵያ ፈተናዎቿን ተቋቁማ በተግባር ማከናወን እንደምትችልና ከተሞቿን ወደ አዲስ የብልጽግና ከፍታ ማሸጋገር እንደጀመረች ለዓለም ያሳየችበት ሕያው ምስክር ነው።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version