እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝኃነት ፀጋ እና ውበት በሆነባቸው ሀገራት፣ ሀገራዊ መግባባት የዘላቂ ሰላም መሠረት ነው።
ሀገራዊ መግባባት፣ የአንድ ሀገር ሕዝቦች፣ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ምሁራንና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በዋና ዋና ብሔራዊ እሴቶች፣ ታሪካዊ ትርክቶች፣ ሕገ-መንግሥታዊ መዋቅሮች እና በሀገሪቱ የወደፊት የጋራ ዕድል ላይ በውይይትና በምክክር የጋራ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ያደርጋል፡፡
ሀገራዊ መግባባት ፈጣንና አስተማማኝ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብ፣ ጠንካራና ተአማኒ ሀገረ-መንግሥት ለመገንባት፣ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር እና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን አስፈላጊ ነው፡፡
በሀገር ውስጥ የሚነሱ አብዛኞቹ ግጭቶችና ጦርነቶች መሠረታቸው የፖለቲካ ልሂቃን የሐሳብና የጥቅም አለመግባባት ነው። ሀገራዊ መግባባት ሲኖር ግን ልዩነቶች በጦር መሣሪያ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ፣ በሰለጠነ የውይይትና የሙግት ባህል እንዲፈቱ በር ይከፍታል። ይህም የዜጎችን ሕይወትና ንብረት ይታደጋል።
ኢትዮጵያ የብዝኃነት ሀገር ናት። ሀገራዊ መግባባት ልዩነትን ማጥፋት ሳይሆን ብዝኃነትን ውበትና ጥንካሬ አድርጎ መቀበል ነው። እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ባህሉ፣ ቋንቋውና ታሪኩ እውቅና እንዳገኘና በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ እኩል ውሳኔ ሰጪ እንደሆነ ሲሰማው፣ ለሀገራዊ አንድነቱ የሚኖረው ታማኝነትና ቁርጠኝነት ይጨምራል።
ሕዝቡና የፖለቲካ ኃይሎች በሕገ-መንግሥቱና በመንግሥታዊ መዋቅሩ ላይ የጋራ ስምምነትና መግባባት ሲኖራቸው፣ የመንግሥት ተአማኒነት ይጨምራል። መግባባት ላይ ሲደረስ የትኛውም መንግሥት በምርጫ ቢመጣ የተቋቋሙት ተቋማዊ ሥርዓቶች የሁሉም በመሆናቸው ሀገራዊ መረጋጋት ይፈጠራል፡፡
ሰላምና መግባባት ሲኖር የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መዋዕለ-ንዋያቸውን ለማፍሰስ ይሰራሉ፡፡ ሀገራዊ መግባባት አስተማማኝ ሰላምን ስለሚፈጥር፣ የመንግሥትንና የሕዝብን ትኩረት ከግጭት ማርገብ ወደ ልማት፣ መሠረተ-ልማት ግንባታ፣ ትምህርትና ወደ ቴክኖሎጂ ማስፋፋት ለማዞር ያስችላል።
በመጪው ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ትልቁን ጉባኤውን የሚያካሂደው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ይህንን የቆየ የልሂቃንና የሕዝብ ክፍተት ለመሙላት የተከፈተ ታሪካዊ የሰላም በር ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመላ ሀገሪቱ ካሰባሰባቸው ግብዓቶች በመነሳት፣ ሕዝቡ በጋራ እንዲመክርባቸውና መግባባት ላይ እንዲደርስባቸው የለያቸውን ስምንት ዋና ዋና ምሰሶዎች ይፋ አድርጓል፡፡
እነዚህም ሀገር ግንባታ እና ሀገራዊ ማንነት ወይም የወል ትርክቶች እና ታሪካዊ ስምምነቶች፤ የፖለቲካ ሥርዓት፤ የመንግሥት መዋቅር እና የመንግሥት ቅርጽ ወይም አወዛጋቢ የሕገ-መንግሥት አንቀጾችን ጨምሮ፤ የፌዴራል ከተሞች ጉዳይ ወይም የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ አስተዳደራዊ ወሰንና መብቶች፤ የተቋማት ግንባታ የሕግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብቶች፤ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ወይም የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች አብሮነት፤ የሙስና እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች እንዲሁም የሰላም ግንባታ እና ደኅንነት መሆናቸውን አሳውቋል፡፡
ሀገራዊ መግባባት የሁሉም ወገኖች እኩል የመደማመጥ፣ የመቻቻልና የአንድን ወገን ጥቅም የመተው እንዲሁም የፖለቲካ ብስለት የሚጠይቅ ሂደት ነው።
በኢትዮጵያ ዘላቂ መግባባትን ለመፍጠር የጋራ ትርክትን፣ ብዝኃነትን ያካተተ አስተዳደር እና ሀገራዊ ጥቅምን የሚያስቀድሙ ተቋማትን መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉትን ታሪካዊ ክስተቶች፣ አወንታዊና አሉታዊ አሻራዎች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መረዳትና ለጋራ መጻኢ ዕድል ማዋል ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ እጆቿን ለሰላም እንደዘረጋች እንድትቀጥል፣ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ አስተማማኝ እንዲሆን እና ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት እንድትገነባ ሀገራዊ መግባባት ወሳኝ ነው።
ሀገራዊ መግባባት ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የጦርነትና የትርክት ፖለቲካን በማስቀረት ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ያግዛል፡፡ ብዝኃነትን ያከበረ እና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነት በመፍጠር ለቀጣዩ ትውልድ የተረጋጋች ሀገር ለማስረከብ ያግዛል፡፡ ይህም የተግባባችና በጠንካራ ኢኮኖሚ ላይ የቆመች ሀገር ለመገንባት ፍቱን ነው፡፡
ሀገራዊ መግባባት የአንድ ወገን ፍላጎት ሳይሆን የሁሉም ዜጎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሃይማኖት ተቋማት ንቁ ተሳትፎና እኩል የመደማመጥ ባህል የሚጠይቅ ታሪካዊ ሂደት በመሆኑ፣ ሁላችንም የምክክር ኮሚሽኑን ታሪካዊ ጉባዔ መካሄድ እና የውይይቱን ውጤት በጉጉት እንጠብቃለን፡፡

