አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግና የተፈጥሮና ታሪካዊ ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚያዊ እሴት ለመቀየር በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በስኬት አከናውናለች።
ይህ በመደመር ፍልስፍና የተመራ ጉዞ ቀደም ሲል ትኩረት ተነፍጓቸው የነበሩ የከተማ መካነ ቅርሶችንና የወንዝ ዳርቻዎችን ወደ ታላላቅ የቱሪስት መስህብነት ቀይሯቸዋል።
ለዚህ መዋቅራዊ ሽግግር ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረውና የዋና ከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ የለወጠው የገበታ ለሸገር ፕሮጀክት ግንባር ቀደሙ ማሳያ ነው።
የገበታ ለሸገር ፕሮጀክት አዲስ አበባን ለአኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ይበልጥ ምቹና ተመራጭ በማድረግ ረገድ ታሪካዊና ቁጥራዊ ስኬቶችን ያስመዘገበ ሲሆን፤ በዚህ ግዙፍ የልማት ንቅናቄ ሥር የተገነቡት ታላላቅ ሥራዎች የከተማዋን የቱሪስት ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ከእነዚህም መካከል የሀገሪቱን ታሪክ፣ ባህልና የተፈጥሮ ሀብት በአንድ ላይ የያዘው ግዙፉ አንድነት ፓርክ የእንስሳት ማቆያ፣ የታሪክ ሙዚየምና የባህል ማዕከላትን አካቶ የተገነባው ፕሮጀክት ቀዳሚ መስህብ ነው።
በእንጦጦ ተራራ ላይ የተገነባውና ከተማዋን ከከፍታ ላይ ለማየት የሚረዱ የመመልከቻ ስፍራዎችና ማረፊያዎች ያሉት እንጦጦ ፓርክም ለስፖርት፣ ለብስክሌት እና ለፈረስ ግልቢያ እንዲሁም ተፈጥሮ ለሚወዱ እጅግ የተመቸ ስፍራ በመሆን የከተማዋን አማራጮች አስፍቷል።
በተጨማሪም በከተማዋ እምብርት የሚገኘው የወዳጅነት ፓርክ በሁለት ምዕራፎች የተገነባ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሰው ሰራሽ ሐይቅ፣ የውኃ ዳንስና ውብ የእግር ጉዞ መንገዶችን የያዘ ሲሆን፣ ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የሳይንስ ሙዚየምን፣ የሠርግ ሥነ-ሥርዓት ማከናወኛዎችንና ትልልቅ የመዝናኛ ስፍራዎችን ያካተተ ነው።
በዚህ በወዳጅነት አደባባይ ምዕራፍ ሁለት ውስጥ ደግሞ የሳይንስ ሙዚየም በቅርጹም ሆነ በውስጡ በያዛቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ዘመናዊ የሆነ የጥናትና ምርምር ማዕከል በመሆን ያገለግላል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ይፋ ከተደረጉበት ጊዜ ጀምሮ በሚሊየን የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ማስተናገድ የተቻለ ሲሆን፤ ይህም ቀደም ሲል ለስብሰባ ብቻ ወደ አዲስ አበባ ይመጡ የነበሩ የዓለም አቀፍ ተቋማት ልዑካን ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ በማስቻሉ የከተማዋ የቱሪዝም ገቢ እንዲያድግ ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል።
ይህ ስትራቴጂካዊ ልማት ከቱሪዝም ባሻገር፣ በቀጥታ ከዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወትና ለኑሮ ተስማሚነት መሻሻል ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሲሆን ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል የቆሻሻ መጣያ የነበሩ አካባቢዎችን ወደ ዘመናዊ መዝናኛ፣ የስፖርት ማዕከላትና የባሕል ምልክትነት ቀይሯቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የገበታ ለሸገር ሌላኛው ስኬት ሕብረተሰቡን በቀጥታ የሥራ ዕድልና የንግድ ትስስር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ሲሆን፤ በፓርኮቹ ግንባታ ወቅትና በአሁኑ ወቅት ባሉ የሥራ ዘርፎች ብዙዎች ዘላቂ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ አድርጓል።
አሁን ላይ ከገበታ ለሸገር ወደ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች በማደግ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ከተሞችንና የቱሪስት መዳረሻዎችን እያነቃቃ የሚገኘው ይህ ንቅናቄ ሀገሪቱ የተጀመሩ ግዙፍ ሥራዎችን በጥራትና በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደምትችል በተግባር ያሳየችበት ሕያው ምስክር ነው።
ይህ ከከተማ አልፎ በሀገር ደረጃ ትልቅ ውጤት ማምጣት የቻለ ወሳኝ ፕሮጀክት ለከተሞች የኢኮኖሚ ትንሳኤና ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማይናወጥ መሠረት የጣለ ወሳኝ ሥራ ነው።
በዮናስ ጌትነት

