አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተፈረሙ ሶስት የፋይናንስ ድጋፍና ብድር ስምምነት አዋጆችን አጸደቀ፡፡
6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ ነው የብድር ስምምነቶችን ያፀደቀው፡፡
ለምክር ቤቱ ከቀረቡት ስምምነቶች መካከል የመጀመሪያው ለዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ የእድገት ልማት ፖሊሲ ማስፈፀሚያ የሚውል የ437 ሚሊየን 400 ሺህ ኤስ.ዲ.አር የብድር ስምምነት ነው፡፡
ሁለተኛው ለማህበረሰብ ተኮር የመሬት አያያዝ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል የ145 ሚሊየን 500 ሺህ ኤስ.ዲ.አር የብድር ስምምነት ነው፡፡
ሶስተኛው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የመስኖ ልማት ለዘላቂ ምርታማነት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የ54 ሚሊየን 600 ሺህ ኤስ.ዲ.አር የብድር ስምምነት አዋጆችን መርምሮ ምክር ቤቱ ማጽደቁን ኢዜአ ዘግቧል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ በዚህ ወቅት÷ የብድርና ድጋፍ ስምምነቶች ኢትዮጵያ የምታከናውናቸው የልማት ተግባራት ምን ያህል ለውጥ እያመጡ እና የህብረተሰቡን ህይወት በተጨባጭ እየቀየሩ መሆናቸውን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙን ይበልጥ በማጠናከር ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችን በመጠንና በጥራት በማሳደግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት አይነተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
የወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ የአርሶና አርብቶ አደሮችን ህይወት ለማሻሻል በሚደረገው ረብርብ ትልቅ የፋይናንስ አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የብድር ስምምነቱ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባትና የመስኖ ልማቶችን ለማዘመን ያግዛል ብለዋል።

