Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአፋር ክልል የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፋር ክልል የ2018 የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል በዛሬው እለት ተጀምሯል፡፡

በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ÷ የአፋር መሬት ማንኛውንም ዓይነት እጽዋት ማፍራት የሚችል ከፍተኛ አቅም እንዳለው በተግባር ታይቷል ብለዋል።

ይህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የክልሉን የተፈጥሮ ሚዛን በአስተማማኝ ሁኔታ ከመጠበቅ ባለፈ፣ ለቀጣይ ትውልድ ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና ጠንካራ መሰረት የሚጥል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ክልሉ በአሁኑ ወቅት እያከናወናቸው ያሉ ዘላቂ የልማት ስራዎች በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርአያነት ሊጠቀሱ የሚችሉና ተሞክሮ የሚወሰድባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በአረንጓዴ ዐሻራ ዘርፍ የተጀመሩ አበረታች ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

ማህበረሰቡ የነገ ተስፋውን ይበልጥ ለማጠናከርና ቀጣይነት ያለው ልማትን ለማረጋገጥ በየአካባቢው በሚከናወኑ የችግኝ ተከላ ስራዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፍም ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Exit mobile version