አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በኮሪደር ልማት የመንግሥታችንን እሳቤዎች፣ የልማታችንን አካታችነት እንዲሁም የሥራችንን ጥራት ማሳየት ችለናል አሉ።
የከተማና መሠረተ ልማት የሴክተር ጉባኤ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው ላይ ሚኒስትሯ እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማት ከተሞቻችንን በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ።
ኮሪደር ከመንገድ፣ ከቁጥር፣ ከመሰረተ ልማት ባሻገር ብዙ ጉዳዮችን አቅፎ የያዘ ኢኒሼቲቭ መሆኑን ገልጸው፤ በኮሪደር ልማት የመንግስታችንን እሳቤዎች፣ የልማታችንን አካታችነት፣ የህልማችንን ግዝፈት እና የሥራችንን ጥራት ማሳየት ችለናል ብለዋል።
በኮሪደር ልማት ከተሞቻችን ብቻ ሳይሆኑ፣ የሥራ ባህላችን በመሰረታዊነት ተለውጧል በማለት ገልጸው፤ ሌሎች ስለኛ ያላቸው አመለካከት ተቀይሯል፣ የመፈጸም አቅማችን አድጓል ሲሉ ተናግረዋል።
ኮሪደር ልማት ለከተሞች ብቻ ሳይሆን ለዘርፉም ጭምር በርካታ ዕድል ይዞ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በከተሞች የኮሪደር ልማት እየተመዘገበ ያለውን ስኬት በገጠር የኮሪደር ልማት አስቀጥለን የሀገራችንን የብልጽግና አይቀሬነት እናረጋግጣለን ነው ያሉት።
የለውጡ መንግሥት ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን የተጀመሩትን ማጠናቀቅ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሆነም አስታውሰዋል።
ዛሬ የምናከብራቸው ስኬቶች የመንግሥታችንን እና የኢትዮጵያን ህዝብ ታታሪነት እና ትጋት ያመለክታሉ ብለዋል።
የሚለማው መንገድና ኮሪደር የበለጠ ትስስር፣ የበለፀገ እና ፍትሃዊ ሀገር የመመስረት ራዕያችን እየተሳካ ስለመሆኑ ማሳያ ነው በማለት ገልጸዋል።
ሕዝቡን በማስተባበር ለሁለንተናዊ ብልጽግና አሻራችንን ማሳረፍ ሀላፊነት ብቻ ሳይሆን ዕድልም ጭምር ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሁሉም አካላት ቅንጅትና መደጋገፍ እጅግ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በቤዛዊት ከበደ

