Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከቡና ምርት ሽያጭ 3 ቢሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በ2018 በጀት ዓመት ከቡና ምርት ሽያጭ 3 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል አሉ።

በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚተገበር ሀገራዊ የቡና ልማት ፓኬጅ መተግበሪያ ሰነድ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

ሚኒስትሩ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ የቡና ልማት ፓኬጅ መተግበሪያ ሰነዱ ኢትዮጵያ በቡና ልማት ያላትን ተጠቃሚነት ያሳድጋል።

በዘርፉ ጥልቅ ምርምር በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ለዚህም የአንድ ዓመት የገበያ ቅድመ ትንበያ ተጠንቶ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።

የቡና ልማት ፓኬጅ መተግበሪያ ሰነዱ በሄክታር የሚገኘውን የቡና ምርት መጠንን መጨመር የሚያስችሉ መመሪያዎችን ማካተቱን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ናቸው።

የሰነዱ ወደተግባር መግባት በ2023 ዓ.ም በሄክታር የሚገኘውን የቡና ምርት ከ8 ወደ 21 ኩንታል ለማሳደግ እንደሚያስችል አብራርተዋል።

ይህም ከቡና ምርት የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ 6 ቢሊየን ዶላር ያደርሰዋል ነው ያሉት።

ሰነዱ የቡና ምርትን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተስማሚ በማድረግ ከዝናብ ጥገኝነት የሚያላቅቁ አሰራሮችን እና ምርታማነትን የሚጎዱ ጉዳዮችን ለይቶ የመፍትሄ ሀሳብ እንዳካተተ ተነስቷል፡፡

የግል ባለሀብቶችን በማሳተፍና ሂደቶችን በመገምገም በየደረጃው መፍትሄ መስጠት የሚያስችሉ ዝርዝር ጉዳዮችን እንደያዘ ተመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ ከ6 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች በቡና ልማት ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን ከወጪ ንግዱም የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ30 በመቶ በላይ የሚሸፍን እንደሆነም በመድረኩ ተነስቷል።

በሔኖክ ለሚ

Exit mobile version