Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኦሮሚያ ክልል የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 65 ነጥብ 9 በመቶ ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ የክልሉ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በፊት ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 65 ነጥብ 9 በመቶ ከፍ ብሏል አለ።

ይህም የሆነው ባለፉት አራት ዓመታት በክልሉ በተከናወኑ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተግባራት መሆኑ ተገልጿል።

ቢሮው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ላይ የተሰሩትን ስራ በመገምገምና በቀጣይ አምስት ዓመታት ለማሳካት በተያዙ ግቦች ዙሪያ ከባለድርሻዎች ጋር በቢሾፍቱ ከተማ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።

በዚህ ወቅት የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አህመድ እድሪስ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉና በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ተዳክሞ በነበረበት ወቅት የተጀመረ ስራ መሆኑን አስታውሰዋል።

ንቅናቄው ወደ ትግበራ ከገባ በኋላ ጥልቅ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎችን ቀርጾ በመተግበር በዘርፉ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ውጤት ማስገኘቱንና እምቅ ሀብትን ከአቅም ጋር በማስተሳሰር ኢንዱስትሪያላይዜሽንን ለማፋጠን ትልቅ አቅም እንደሆነ አንስተዋል።

ባለሀብቶችን በመሳብ ከ158 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን እንዲያለሙ መደረጉን ገልጸው፤ በተኪ ምርት ከ7 ቶን በላይ ምርት በማምረት ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ ማስቀረት ስለመቻሉም ጠቁመዋል።

ለሚስተዋሉ ውስንነቶች በቀጣይ መፍትሄ ለማበጀት የውይይት መድረኩ አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል፡፡

በታምራት ደለሊ

Exit mobile version