Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኮሪደር ልማቱ የጀጎል ቅርስን ከአደጋ በመታደግ ለጎብኚዎች ምቹ አድርጓል – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮሪደር ልማቱ የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስን ከአደጋ በመታደግ ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ምቹ አድርጓል አሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በ4ኛው ዙር የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ መልሶ ማልማት የተከናወኑ ከ9 ኪ.ሜ በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን መርቀዋል።

አቶ ኦርዲን በድሪ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በኮሪደር ልማት ስራዎች ቀደም ሲል የቆሻሻ መጣያና የወንጀል መሸሸጊያ የነበሩ ስፍራዎችን መልሶ በማልማትና በማስዋብ ተመራጭ የመኖሪያና የመዝናኛና ስፍራ ማድረግ ተችሏል።

ከመንግስት ተጨማሪ በጀት ሳይመደብ የወል ትርክት እሳቤን ባነገበ መልኩ የተሰራው ስራ የአመራር ቁርጠኝነትና የህዝብ አንድነት እንዲሁም የዳያስፖራና የሌሎች አካላት ርብርብ በተግባር የታየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ገልጸው፥ ፕሮጀክቶቹን በመጠበቅና በመንከባከብ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም በክልሉ የተገኙ ስኬቶችን በማላቅ የሕዝብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች እውን ለማድረግ መንግስት በላቀ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

በተስፋዬ ኃይሉ

Exit mobile version