አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝቡን የመረጃ ፍላጎት ለማሟላት መረጃን ማዘመንና ዘመናዊ ዳታ መጠቀም ይገባል አሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለስ፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የፌዴራል ተቋማት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የጋራ መድረክ ተካሂዷል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ መድረኩ ተቋማዊ የመረጃ ተደራሽነት ክፍተቶች ላይ በጥልቀት በመወያየትና ገንቢ ሐሳቦችን በመለዋወጥ ለቀጣይ ስኬታማ ሥራዎች ታላቅ ስትራቴጂያዊ ግብዓት ለመሰብሰብ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በየተቋማቱ ያለውን የመረጃ ፍሰት ፍጥነት፣ ጥራትና ዘመናዊ የዲጂታል ተግባቦት ሥርዓት ማዘመን እንደሚገባ ገልጸው፥ ለዘርፉ ስኬት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን አመራርና ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
ሕዝቡ በሳይንሳዊ መንገድ የሚመራ፣ ወቅቱን የዋጀና እውነተኛነቱ የተረጋገጠ መረጃ ይፈልጋል ያሉት ሚኒስትሯ፥ ለዚህም የኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሀገራዊ መረጃዎችን በሚገባ በመተንተንና በማደራጀት ተደራሽ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
መረጃ ትልቅ ሀገራዊና ተቋማዊ ሀብት መሆኑን በጥብቅ በመገንዘብ መረጃ ለሕዝብ የሚደርስበትን አግባብ በመረጃ አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችና ጥንካሬዎችን በየጊዜው እየለዩና እየገመገሙ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

