አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዩኒቨርሲቲዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማበልጸግ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል መፍጠር እንዲችሉ እየተሰራ ነው አለ የትምህርት ሚኒስቴር፡፡
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በዋናው ግቢ፣ በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና በልዕለ ህክምና ካምፓስ የተገነቡ ተግባር ተኮር ፕሮጀክቶችን አስመርቋል፡፡
ዛሬ ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል በቴክኖሎጂ የበለጸገ ዘመናዊ ቤተ ሙከራ፣ ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎች፣ ዘመናዊ የመረጃ ማዕከልና የሰራተኞች የጋራ መኖሪያ ቤቶች ይገኙበታል፡፡
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አወል ሰይድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ዩኒቨርሲቲው በተግባር ተኮር ትምህርት ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል እያፈራ ይገኛል፡፡
በዛሬው ዕለት የተመረቁት ፕሮጀክቶችም ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠውን ተግባር ተኮር ትምህርት በቴክኖሎጂ ለማጠናከር የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የተቋማት አደረጃጀትና አመራር ዴስክ ኃላፊ አቶ ጫኔ አደፍርስ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርስቲዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማበልጸግ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል መፍጠር እንዲችሉ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች መሰረተ ልማትና ግብዓት በማሟላት የእውቀት፣ ክህሎትና የምርምር ማዕከል እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ የቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉና በቴክኖሎጂ የበለጸጉ መሆናቸውን ገልጸው፥ የዩኒቨርስቲውን ተግባር ተኮር ትምህርት ያረጋግጣሉ ነው ያሉት፡፡
በከድር መሀመድ

