አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ በመንገድ ትራፊክ ደህንነት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 10 ሺህ በጎ ፈቃደኞች ይሰማራሉ አለ የከተማዋ የሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን::
በአዲስ አበባ ከተማ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት “በጎነት ለአዲስ አበባ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዘርፎች እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በዛሬው ዕለትም የ2018 ዓ.ም የመንገድ ትራፊክ ደህንነት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ይመር ከበደ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችና አገልግሎቱን ተቋማዊ የማድረግ ሥራ አመርቂ ውጤት ተገኝቷል፡፡
በተለይም የትራፊክ አደጋዎችን በመከላከልና በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው ÷ በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 10 ሺህ ዜጎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡
በጎ ፈቃደኞቹ በከተማዋ በተለዩ 141 አደባባዮችና የትራፊክ እንቅስቃሴ የሚበዛባቸው አካባቢዎች የሚሰማሩ ሲሆን ÷ ሕብረተሰቡ በጎ ፈቃደኞችን በመታዘዝና በመተባበር እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የትራፊክ አደጋን አስከፊነት በማስተማርና በመከላከል በአደጋው የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ እንደሚገባም ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
በጀማል አሕመድ

