አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ሲያልፍ በነበረ የፓናማ መርከብ ላይ የተሰነዘረውን የድሮን ጥቃት ተከትሎ በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት ፈጽማለች።
አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ በንግድ መርከቦች ላይ ለቀጠለው ትንኮሳ በትናንትናው ዕለት ምላሽ ለመስጠት በኢራን ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟ ተመላክቷል፡፡
አሜሪካ እና ኢራን አንዳቸው በሌላኛው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎም ሀገራቱ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ይገኛሉ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ÷ ቴህራን ፈጽሞ የማትማር መሆኗን ጠቅሰው የተጀመረውን ወታደራዊ ሥራ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ሊገደዱ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
ይህ ከተከሰተ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ አይቀጥልም ሲሉም የሪፐብሊኩ ሕልውና አደጋ ላይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የአሜሪካ ጦር ባወጣው መግለጫ ÷ ኢራን የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት እንድታከብር ዕድል ተሰጥቷት ነበር፤ ይሁን እንጂ የሀገሪቱ ኃይሎች በንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ስምምነቱን ለመጣስ መርጠዋል ብሏል።
በዚህም የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶች በሆርሙዝ ሰርጥ አካባቢ በሚገኙ 10 የኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ነው ያስረዳው፡፡
እነዚህ ጥቃቶች ወታደራዊ ቁሳቁሶች፣ የመገናኛ ዘዴዎች፣ የአየር መከላከያ ጣቢያዎችና የድሮን ማከማቻ ማዕከላት ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ ÷ አሜሪካ በኢራን የባሕር ዳርቻ ምሽጎች ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ለሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ለጥቃቱ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠትም በኩዌትና ባህሬን በሚገኙ ስምንት ቁልፍ የአሜሪካ መሰረተ ልማቶች ላይ የባላስቲክ ሚሳኤልና የድሮን ጥቃት መፈጸሙን አብራርቷል፡፡
በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት ኢራን በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ የሚያልፉ መርከቦችን የመቆጣጠር መብት እንዳላት ጠቅሶ ÷ በቀጣይ ጥሰት በሚፈጽሙ መርከቦች ላይ ጠንካራ ርምጃ እንደሚወሰድና ማንኛውም ዓይነት ትንኮሳ ቢሰነዘር አስተማማኝ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ አስጠንቅቋል።
በሌላ በኩል የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአሜሪካ ኃይሎች ቅርበት ባላቸው ኢላማዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት መፈጸሙን ገልጾ ÷ ለተፈጠረው ወታደራዊ ውጥረትና አለመረጋጋት አሜሪካን ተጠያቂ አድርጓል።
የሀገራቱ ጦርነት ለነዳጅና ጋዝ ጭነቶች ቁልፍ መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ ሰርጥ በተደጋጋሚ እንዲዘጋ በማድረግ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ይገኛል፡፡
በዮናስ ጌትነት

