አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲያገኙ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ።
የቢሮው ኃላፊ አሕመድ ኢብራሂም እንዳሉት ÷ በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረግ የውጭ ሀገር የሥራ ጉዞ በዜጎች ሕይወትና አካል ላይ እያደረሰ ያለው አስከፊ ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡
ቢሮው በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረግን የሥራ ጉዞ ለመከላከል ሕጋዊ የሥራ ስምሪት አሰራርን በስፋት ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ማንኛውም ዜጋ ፍላጎቱንና መብቱን የሚያስከብሩ ሕጋዊ አማራጮችን ብቻ በመጠቀም ራሱን ከጉዳት፤ ቤተሰቡን ደግሞ ከስጋት ሊጠብቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ሃላፊው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
ዜጎች በየደረጃው በሚገኙ ማዕከላት ስልጠናዎችን እንዲወስዱ በማድረግ መብትና ግዴታቸውን ተገንዝበው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ሐስና መሃመድ በበኩላቸው ÷ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ጉዞ ሳቢያ ለሚደርሱ ዘርፈ ብዙ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ግንባር ቀደም ተጋላጭ የሆኑት ሴቶች ናቸው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ሴቶች ከእነዚህ አስከፊ አደጋዎች ራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪትን በሕጋዊ መንገድ ብቻ ሊያከናውኑ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
መንግሥት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዜጎችን መብት፣ ክብርና ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማስከበር ስልታዊ የፖሊሲ ርምጃዎችን ወስዶ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ሴቶች የተዘጋጁትን ሰፊ የማሰልጠኛ ዕድሎች በአግባቡ በመጠቀም ሙያዊ ብቃታቸውን አሳድገውና ተወዳዳሪ ሆነው ከስጋት ነጻ በሆነው ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በአሊ ሹምባሕሪ

