አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የክልሉ ሕዝብ በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ጉዳዩን አስመልክተው ባስተላለፍት መልዕክት ÷ በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን አንስተዋል፡፡
በደን መራቆት የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ባለፉት 7 ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በክልሉ ከ28 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው ÷ ከእነዚህ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በክልሉ የነበረው 17 በመቶ የደን ሽፋን ወደ 29 በመቶ ማደጉን ነው አቶ ሽመልስ አጽንኦት የሰጡት፡፡
በክልሉ በዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በ1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ ከ5 ቢሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል መታቀዱን አመልክተዋል፡፡
በክልሉ የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በነገው ዕለት እንደሚጀምር ጠቁመው ÷ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

