አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት የከተማ ባህልንና የነዋሪዎችን ማኅበራዊ ሕይወት የቀየረ ታሪካዊ ስኬት ነው አሉ በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክትን በትላንትናው ዕለት መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል፡፡
አቶ ሞገስ ባልቻ ፕሮጀክቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ፥ ፕሮጀክቱ ለዘመናት በአዲስ አበባ ከተማ ተዘንግቶ የነበረውን የተፈጥሮ ጸጋ ወደ ታላቅ የሕዝብ ሃብትነት የለወጠና የከተማዋን ነዋሪዎች የአኗኗር ዘይቤ በአዲስ መልክ የገነባ ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
ኃላፊው ቀደም ሲል የቀበና ወንዝ አካባቢ በከባድ ሽታ፣ ወጣ ገባ የመሬት አቀማመጥና በተወሳሰበ የሕዝብ አሰፋፈር ምክንያት ለሰው ልጅ ጤና ጠንቅና ለከተማዋ ስጋት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ግን እነዚህን ውስብስብና ፈታኝ መሰናክሎች በቁርጠኝነት በማለፍ፣ ቦታው ለአዛውንቶች፣ ለወጣቶችና ለቤተሰቦች ልዩ የአእምሮ እረፍትና የሕሊና ሐሴት የሚሰጥ አስተማማኝ ማዕከል ሆኗል ነው ያሉት፡፡
አዲስ አበባ ሰፊ የውሃ ጸጋ እያላት በሰው ሰራሽ ብልሽቶች ታፍና መቆየቷን ጠቅሰው ÷ ይህ ፕሮጀክት ግን ከተማዋን ወደ ዓለም አቀፍ የቱሪስት ማዕከልነት ከፍ የሚያደርግ አዲስ አቅም መፍጠሩን አስረድተዋል።
በአካባቢው የሚኖሩ አዛውንቶች ከዘራቸውን ይዘው በነፃነት የሚንሸራሸሩበት፣ እንስቶችና ቤተሰቦች ቁጭ ብለው የሚመካከሩበትና የውሃውን ድምፅ እያዳመጡ አእምሯቸውን የሚያድሱበት ምቹ ባህል መፈጠሩን አመልክተዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ

