አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቬንዙዌላ ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የሟቾች ቁጥር 1ሺህ 450 መድረሱን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ አስከፊ አደጋ በተዓምር የተረፉት እናት እና የ18 ቀን ጨቅላ ልጇ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆነዋል፡፡
አደጋው በተከሰተበት ላ ጓይራ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ዳያና ፓቲኖ ከአደጋው በፊት 8ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ውስጥ እንደነበረች ትናገራለች፡፡
ህንጻው መወዛወዝ ሲጀመር ወዲያው ዩዋን ዴቪድ የተባለውን የ18 ቀን ጨቅላ ልጇን ለመጠበቅ ወደ ክፍሏ መሮጧን ገልጻለች፡፡
ይሁን እንጂ ለረጅም ሰዓት በቆየው አደጋ ህንፃው መደርመሱንና እሷ እና ልጇ ለአንድ ሰዓት ያህል በህንጻው ፍርስራሽ ውስጥ ለመቆየት ተገድዳለች፡፡
ግራ እግሯ በህንፃው ኮንክሪት ውስጥ በመግባት መንቀሳቀስ እንዳትችል ያደረጋት ሲሆን በዚህም የነፍስ አድን ሰራተኞች ሳያገኟት ለረጅም ጊዜ በሞትና ህይወት መካከል ሆና መቆየቷን ገልጻለች፡፡
ልጄ ሞቷል ብዬ ነበር፤ በህይወት መኖሩን ለማረጋገጥ አፍንጫዎቹን እየነካሁ እስትንፋሱ መኖሩን ሳረጋግጥ ነበር የምትለው ይህቺ እናት፥ እንደማልተርፍ ቢሰማኝም ከልጄ በፊት አልሞትም እያልኩ ለራሴ እነግረው ነበር በማለት የነበረችበትን ሁኔታ አስረድታለች፡፡
እናት ዳያና ፓቲኖ የነፍስ አድን ሰራተኞችን ድምፅ ስትሰማ እርዱኝ እያለች ስትጣራ እንደነበር ተናግራለች፡፡
በፍርስራሽ ውስጥ ለአንድ ሰዓት ያህል ከቆየች በኋላ የነፍስ አድን ሰራተኞች ደርሰው ከሞት አፋፍ እንዳዳኗት ለቢቢሲ ተናግራለች፡፡
በአደጋው እናት ዳያና እግሮቿ ላይ እንዲሁም የ18 ቀን ጨቅላ ልጇ ዩዋን ዴቪድ በፊቱ ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸው በካራካስ ሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ ሲሆን፥ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ

