አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቱሪዝም ዘርፍ አስደናቂ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ 19 ቅርሶችን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር ናት፡፡
ለዘመናት የተዘነጉ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ተገቢውን ጥገናና እድሳት እንዲያገኙ በማድረግ በተሰራው ስራ ውጤት ማምጣት ተችሏል፡፡
ብሔራዊ ቤተ መንግሥት፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ ጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግሥት፣ የሐረር ጁገል ግንብ እና የሶፍ ኡመር ዋሻን ጨምሮ በርካታ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ታድሰው የቱሪዝም ገቢን እያሳደጉ ይገኛሉ።
በርካታ መስህቦች በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ የቀረቡ ሲሆን በጣና ሐይቅ የሚገኙ ደሴቶችንና የአልነጃሺ ታሪካዊ መንደርን ለማስመዝገብ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
ይህ የቅርስ ጥበቃና ልማት ሥራ በመንግስት በኩል ቱሪዝምን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ በመለየት ዘርፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ቁልፍ ተግባራት ተከናውነዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት የተተገበሩት የገበታ ለሸገር፣ የገበታ ለሀገር እና የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋት ረገድ ትልቅ አቅም ሆነዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማስፋት ባለፈ የግሉ ዘርፍ በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ላይ በስፋት እንዲሳተፍ እና ተወዳዳሪነቱ እንዲጠናከር ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል።
በመዲናዋ የተሰሩት የልማት ስራዎች የሀገሪቱን የቱሪዝም አድማስ በተጨባጭ አሳድገዋል፡፡
የአንድነት፣ የእንጦጦና የሸገር ፓርኮች፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያና ዘመናዊ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ከተማዋን ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ማራኪ አድርገዋታል።
በመዲናዋ ብቻ በተያዘው ዓመት ከ150 በላይ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንሶች የተካሄዱ ሲሆን፤ በ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ 153 ጉባዔዎች መካሄዳቸው ከተማዋ የዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ማዕከል እየሆነች መምጣቷን የሚያረጋግጥ ነው።
በተያዘው በጀት ዓመት 9 ወራት ውስጥ ብቻ ኢትዮጵያ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን የውጭ ጎብኚዎችን ተቀብላ በማስተናገድ ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማግኘት ችላለች።
የሀገር ውስጥ ቱሪዝም በከፍተኛ ደረጃ መነቃቃት ያሳየ ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች 60 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የቱሪዝም ማዕከል ኢትዮጵያን በ2025 እና 2026 በዓለም ፈጣን የቱሪዝም እድገት እያሳዩ ከሚገኙ ሀገራት መካከል መድቧታል።
የዓለም የጉዞና የቱሪዝም ምክር ቤት ሀገሪቱ በ2025 በጎብኚዎች ቁጥር ያሳየችውን የ15 በመቶ ዕድገት በመጥቀስ ተስፋ ሰጪ ከሆኑ የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዷ መሆኗን አመልክቷል፡፡
ከዚህ ባሻገር በዓለም የጉዞ ሽልማት በ2025 እና 2026 በአፍሪካ ቀዳሚ መዳረሻ ዘርፍ ለመታጨት በቅታለች።
እነዚህ ስኬቶች የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ በመንግስት ቁርጠኝነት፣ በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እና በሕዝብ አቅም ፈጣንና ውጤታማ ሽግግር እያደረገ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነው፡፡
በዮናስ ጌትነት

