አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የእንጦጦ-ቀበና የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከንቲባዋ የእንጦጦ – ቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክትን በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው የእንኳን ደስ አላችሁ እና የምስጋና መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ፕሮጀክቱ ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ደማቅ አሻራ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማዋ እየተገነቡ ያሉት ግዙፍ መሰረተ ልማቶችና አዳዲስ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሚከናወኑት በከተማ በጀት እንጂ በብድር ወይም በእርዳታ አይደለም ሲሉ አስገንዝበዋል።
የቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክትም በምንም ዓይነት የውጭ ብድር ወይም እርዳታ እንዳልተሰራ ጠቁመው÷ ስኬቱ የከተማዋ ግብር ከፋዮች፣ የገቢ ሰብሳቢና የፋይናንስ ተቋሞች አንድ ላይ ተደምረው በትብብር ያሳኩት ልማት ነው ብለዋል።
ይህ እጅግ ውብና ማራኪ የመዝናኛና ጤና መጠበቂያ ሆኖ የተጠናቀቀው የቀበና ወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት በዋናነት የተሰራው ለከተማዋ ነዋሪዎች በመሆኑ እንዲጎበኙትና እንዲዝናኑ ጋብዘዋል፡፡

