አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለበርካታ ዓመታት አዲስ አበባን ያጨናነቃትና የነዋሪዎቿ ጤና ስጋት ሆኖ የቆየው የወንዞች መበከል ዛሬ በእንጦጦ-ቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት አማካኝነት ታሪኩን ቀይሯል።
ይህ ፕሮጀክት ተራ የውበት ስራ ሳይሆን አዲስ አበባ ወደፊት ለምትከተለው ዘመናዊ የከተማ ፕላኒንግ አዲስ ፍልስፍና የፈጠረ ታሪካዊ ክስተት ሆኗል።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያውያን መሃንዲሶችና አርክቴክቶች የተነደፈና የተገነባ መሆኑ ለሀገር በቀል ባለሙያዎችም ትልቅ የአቅም ማሳያ ነው።
የወንዙን ተፈጥሯዊ መስመር ሳይለቁ የተገነቡት የጎርፍ መከላከያ ግንቦች፣ የእግረኛና የሳይክል መንገዶች የተፈጥሮን ይዘት ሳይበክሉ ዘመናዊነትን ማላበስ እንደሚቻል በተግባር አሳይተዋል።
በተለይም በወንዙ ላይ የተገነቡት መሸጋገሪያ ድልድዮች እና ተንጠልጣይ ድልድዮች የምህንድስና ጥበብን ከማሳየታቸው ባለፈ፤ ቀደም ሲል በወንዙ ምክንያት ተለያይተው የነበሩትን ማኅበረሰቦችና ሰፈሮች በአዲስ መልክ አስተሳስረዋል።
ፕሮጀክቱ ያካተተው 1 ትልቅ ግድብ፣ 16 አነስተኛ ግድቦች፣ 3 ቼክ ዳሞች፣ 1 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሃይኪንግ፣ 20 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የወንዝ ድጋፍ ግድግዳ የጎርፍ አደጋን ከመከላከል ባለፈ፣ ከተማዋ ዓመቱን ሙሉ የማይቋረጥ የውሃ ጸጋ እንዲኖራት ያደርጋሉ።
በቀጥታ ወደ ወንዙ ይገባ የነበረውን ቆሻሻ ያስቀረው 19 ነጥብ 13 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ እና የጎርፍ ማስወገጃ መስመር የወንዙን ሕይወት መልሶ ቀስቅሶታል።
እንዲሁም ፕሮጀክቱ ያካተተው 59 ነጥብ 7 ሄክታር የሚሸፍን የአረንጓዴ ልማት እና የተተከሉ የፍራፍሬ ዛፎች የከተማዋን የሙቀት መጠን በመቀነስ ረገድ የላቀ ስነ-ምህዳራዊ ፋይዳ አላቸው።
ይህም በዘመናዊ ከተሞች ፕላን ውስጥ ውሃን (ሰማያዊ) እና አረንጓዴ ተክሎችን (አረንጓዴ) በማቀናጀት “Blue Green Infrastructure” የሚባለው ጽንሰ-ሐሳብ በዚህ ፕሮጀክት ማሳካት የተቻለበት ነው።
ቀደም ሲል የቀበና ወንዝ ዳርቻዎች ሕገ-ወጥ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ እና ጥጋጥጋቸው ለወንጀል ምቹ የሆኑ አካባቢዎች በፕሮጀክቱ ገጽታው ተቀይሮ የማኅበራዊ መስተጋብር መፍጠሪያ ምቹ ስፍራ ለመሆን በቅቷል።
የ9 የስፖርት ሜዳዎች፣ የካፌዎች፣ የሬስቶራንቶች እና የ23 ዘመናዊ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች መገንባት ማኅበረሰቡ በነፃነት የሚገናኝበት፣ አዛውንቶች የሚንሸራሸሩበት እና ሕፃናት የሚጫወቱበት የሕዝብ የጋራ ስፍራ ባህል በከተማዋ እንዲያብብም አድርጓል።
ፕሮጀክቱ ጥንታዊ ማንነትን ከዘመናዊ የሥራ ባህል ጋር በማቀናጀት አፍሪካውያን ከተሞቻቸውን በራሳቸው አቅም ማደስ እንደሚችሉ አሳይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ አዲስ አበባ ከዚህ በላይ እምቅ አቅም አላት፤ ብዙ መሰራት የሚገባቸው እና መታየት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ።
ቀበና አሁን ያለውን መልክ እና ውበት ሊይዝ ይችላል ብሎ አስቀድሞ ማሰብ እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ፤ ማየት ሲቻል ስራ ይከተላል ብለዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ

