Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመደመር እሳቤ የተገለጠበት የወንጪ-ደንዲ ኢኮ-ቱሪዝም

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የወንጪ-ደንዲ ኢኮ-ቱሪዝም ፕሮጀክት ዋነኛ የቱሪዝም መስህብ ከመሆን ባለፈ የዜጎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን አረጋግጧል፡፡
ከአዲስ አበባ በ150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ወንጪ ከባህር ጠለል በላይ 3 ሺህ 380 ሜትር ከፍታ ላይ ሲገኝ ሐይቅና ፍል ውሃን ጨምሮ እጅግ ማራኪ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶችን የያዘ ድንቅ የቱሪስት መዳረሻ ነው።
በአካባቢው የሚገኘው ደንና በውስጡ ያሉት ብርቅዬ አዕዋፋት ዝማሬ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡና አዕምሮን ዘና የሚያደርጉ ናቸው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ተጀምረው እውን ከተደረጉ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የወንጪ ፕሮጀክት ቱሪስቶችን በስፋት እየሳበ ይገኛል።
የአካባቢው ማህበረሰብም የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ተግባራትን ያከናውናሉ። በዚህም በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ባህልና እሴትን ለማስተዋወቅ እየተጠቀሙበት ነው።
ከወሊሶ አምቦ፤ ከወንጪ ደንዲ፤ ከደንዲ አስጎሪ ሰፊ የሆነ ቦታ ላይ በምዕራፍ ተከፋፍሎ እንዲገነባ የተቀረጸ ሰፊ ራዕይ ያለው ትልቅ ሀገራዊ የልማት ዐሻራ የሆነው ፕሮጀክቱ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
የፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት ብቻ ከ10 ሺህ ለሚበልጡ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ ከቱሪስት መዳረሻነት ባሻገር ለአካባቢው የማያቋረጥ የሥራ ዕድልና ልማት እያስገኘ ነው።
ለአብነትም በ22 ማኅበራት ለተደራጁ ከ560 የሚበልጡ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተሰርቷል።
ከአዲስ አበባ 135 ኪሎ ሜትር ርቀት ከወሊሶ-አምቦ መንገድ መሃል ላይ በእሳተ ጎመራ የተፈጠረው ወንጪ ሐይቅ ዙሪያ ገባውን አረንጓዴ በለበሱ ድንቅ ተራራዎች የተከበበ ውብ ስፍራ ነው።
በ14ኛው ክፍለ ዘመን የተተከለውን ታሪካዊና ጥንታዊውን ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ያቀፈው ዝምተኛው ወንጪ ሐይቅ÷ እምቅ ብዝሃ-ሕይወት አለው።
ይህ ድንቅ የተፈጥሮ ጸጋ በዓለም ቱሪዝም ድርጅት የ2021 ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሽልማትን አሸንፏል።
ባህላዊና ተፈጥሯዊ ጸጋዎችን የታደለው ወንጪ ሐይቅ የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር መሰኘቱ ለዘላቂ የቱሪዝም ልማትና ተጠቃሚነት ፋይዳው ጉልህ ነው፡፡
በፕሮጀክቱ ሆቴሎች፣ ባህላዊ ሎጅ፣ ሬስቶራንትና የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ወደ ወንጪ ሐይቅ የሚወስደው የአስፋልት መንገድ፣ ወንጪና ደንዲ ሐይቆችን የሚያገናኝ የአስፋልት መንገድ ተገንብቶለታል።
በተጨማሪም የኤሌክትሪክ መሠረተ- ልማት፣ የጤና ማዕከል፣ ትምህርት ቤቶች፣ የቴሌኮም ማሻሻያ ፕሮጀክት፣ የአትሌቶች መንደርን ጨምሮ የተለያዩ ግንባታዎች ተሟልተውለታል።
የመደመር ዕሳቤ በተጨባጭ የተገለጠበት የወንጪ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት፤ የአካባቢን የተፈጥሮ ሀብት በልዩ ጥበብ እና ስራ በማልማት ውበቱን እና መስህብነቱን ከፍ አድርጎ የሀገር ገጽታ እና ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ አስተዋጽኦ ማኖር ጀምሯል።
በአቤል ነዋይ
Exit mobile version