አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዳታ አዲስ ሀብት በመሆን የኢኮኖሚ፣ የደህንነት እና የልማት መሰረት ሆኗል።
ሀገራት የዜጎቻቸውን፣ የመንግሥታዊ ተቋማትን እና የቢዝነስ ተቋማትን ዳታ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ማስተዳደርና መቆጣጠር የብሔራዊ ሉዓላዊነት አካል አድርገው እየተመለከቱት ነው፡፡
የዳታ ሉዓላዊነት ማለት አንድ ሀገር በድንበሯ ውስጥ የሚመረት፣ የሚሰበሰብና የሚከማች ዳታ በሀገሪቱ ሕግና ደንብ መሰረት እንዲተዳደር የሚያስችል ሥርዓት ነው።
ይህም የዜጎችን መረጃ መጠበቅ፣ የመንግሥት የደህንነት መረጃዎችን መጠበቅ እና ዳታ ለሀገራዊ ልማት እንዲውል ማድረግን ያካትታል።
የመንግሥት መረጃዎች፣ የመከላከያ ሥርዓቶች እና የዜጎች መረጃ ከውጭ ጥቃት ወይም ከህገ ወጥ ጥቅም እንዲጠበቁ የዳታ ሉዓላዊነት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ዳታ በአግባቡ ሲተዳደር ለንግድ፣ ለግብርና፣ ለጤና እና ለትምህርት ዘርፎች ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡
የግል መረጃ በህጋዊ መንገድ ለመሰብሰብ እና ለመጠቀም ግልጽ ሥርዓት መኖሩ የዜጎችን እምነት ያጠናክራል፡፡ ይህም ዲጂታል አገልግሎቶችን ለመጠቀም ያበረታታል።
ትክክለኛ እና የተደራጀ ዳታ መንግሥት በማስረጃ ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ የሚያስችል ሲሆን የጤና፣ የትምህርት፣ የታክስ፣ የመሬት አስተዳደር እና ሌሎች አገልግሎቶችን ውጤታማ ያደርጋል።
ጠንካራ የዳታ ሉዓላዊነት ለመገንባት የሀገር ውስጥ ዳታ ማዕከላትን መገንባትና ማስፋፋት፣ የሳይበር ደህንነት አቅምን ማሳደግ፣ በዳታ ሳይንስ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሰው ኃይል ማፍራት፣ የዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፋት ላይ በትኩረት መስራት አስፈላጊ ነው፡፡
የዳታ ሉዓላዊነት መኖሩ የብሔራዊ ደህንነትን ከማጠናከር ባለፈ የኢኮኖሚ እድገትን፣ የዜጎች መብትን እና የመንግሥት ተቋማት ቅልጥፍናን እንደሚያሳድግ ይታመናል፡፡
ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የዳታ ሉዓላዊነትን እንደ ብሔራዊ ስትራቴጂ መመልከት ያስፈልጋል።
ዳታን በአግባቡ የሚያስተዳድር ሀገር በዲጂታል ዘመን የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነቱን፣ የፖለቲካ መረጋጋቱን እና የዜጎችን ደህንነት በተሻለ ሁኔታ ማረጋገጥ ይችላል።
በአመለወርቅ ደምሰው

