Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቅርሶቻችን የጋራ በረከቶቻችን እንጂ የዕዳ ምንጭ አይደሉም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ቅርሶችና የተፈጥሮ ሀብቶች የጋራ በረከቶቻችን እንጂ የዕዳ ምንጭ አይደሉም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር” በሚል በቱሪዝም ዙሪያ ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ግዙፍ አቅም በመጠቀም የዜጎችን ሕይወት መቀየርና የሀገርን ገጽታ መገንባት ይገባል፡፡

ለዚህም የቅርሶችን ታሪክ ከሰፈርና ከመንደር አስተሳሰብ አውጥቶ የጋራ ትርክት መገንባት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ ቀደም ቅርሶችን እንደ በረከት ሳይሆን እንደ ዕዳ የመቁጠር ስህተት እንደነበር ጠቁመው ይህንን ጎጂ አመለካከት በመስበር “ታሪኩም፣ ቅርሱም የሁላችንም የጋራ ሀብት ነው” የሚል ብሔራዊ እሳቤ መገንባት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘናት ያሉትን ድንቅ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ሀብቶች በማንሳት ኢትዮጵያ የሰው ዘር፣ የቡና እና የዓለም የድል ታሪክ መገኛ መሆኗንም አንስተዋል።

የሶፍ ኡመር ዋሻ የከፍተኛ ጥንታዊ ሥልጣኔ ማሳያ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሶፍ ኡመር እስከ ቦሳሶ የሚያገናኝ ጥንታዊ መስመር እንደነበረና በዋሻው ውስጥ የዛሬ 800 ዓመት የነበረ መስጂድና ሰው ሰራሽ ሐይቅ እንደሚገኝበት አብራርተዋል።

አንዳንዶች “የውሃ ዋሻ” ብቻ እንደሆነ አድርገው የሚያቀርቡትን የተሳሳተ መረጃ በማረም ዋሻው ውስጥ ምንም ውሃ የሌለባቸውና ጥንታውያን ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ሥልጣኔያቸውን ያሳዩባቸው ገና ያልተጠኑ በርካታ የታሪክ ክፍሎች እንዳሉ አመልክተዋል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ የሆነችውን የሉሲ (ድንቅነሽ) ታሪክ፣ የኤርታሌ ንቁ እሳተ ጎመራ፣ እና የዳሎልና የደንከል አስደናቂ ተፈጥሮዎችን ያቀፈች ሀገር መሆኗን አውስተዋል።

የአርባ ምንጭ የጫሞና አባያ ሐይቆችን፣ የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ፣ የዶርዜ ህዝቦች የአፕል ልማትና ባህላዊ አኗኗር፣ እንዲሁም 40 የሚሆኑት አስደናቂ የውሃ ምንጮች የኢትዮጵያ ትልቅ ውበት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተፈጥሮ ሃብቶቻችን እና ቅርሶቻችን ማንኛውም ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ ሊኮራ ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ተፈጥሮን ለጥቅም ለማዋል የሄዱበትን ጥበብ የሚያሳይና ለመደነቅ የግድ ኢትዮጵያዊ መሆን የማይጠይቅ የዓለም ቅርስ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

ይህንን ታላቅ ሀብት ለዓለም ገልጦ ማስተዋወቅ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዚህም የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ የመንገድ፣ የአገልግሎት ተቋማት ግንባታና ኢንቨስትመንት በማከናወን የኢትዮጵያን እውነተኛ አቅም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማስተዋወቅ ሥራን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን አቅም በተሟላ መልኩ በጋራ በማልማት ከተጠቀምንበት የብዙ ዜጎችን ሕይወት በከፍተኛ ደረጃ መቀየር ይቻላል ነው ያሉት፡፡

በሶስና አለማየሁ

Exit mobile version