የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎች በውጭ ሀገር ክብራቸው፣ መብታቸውና ደኅንነታቸው ተጠብቆ በሕጋዊ መንገድ እንዲሠሩ በርካታ አሠራሮችን ዘርግቷል።
ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀምና የሁለትዮሽ ስምምነቶችን በመፈረም ሂደቱ ፈጣንና ግልጽ እንዲሆን ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ዜጎች በሕገ-ወጥ ደላሎች እየታለሉ ለከፍተኛ አደጋና ለሞት እንዳይዳረጉ ለመከላከል፣ መንግሥት ዘርፉን በልዩ ትኩረት በመምራት ላይ ይገኛል።
ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን ለማቀላጠፍ የሥራ ስምሪት ማሻሻያና የሪፎርም እርምጃዎችን አድርጓል፡፡
ከእነዚህ ውስጥም የመጀመሪያው የጉዞ ሂደቱን ከሰው ንክኪ ነፃ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ሂደት አጭበርባሪዎችን ለመቆጣጠር ሲባል ምዝገባው ሙሉ በሙሉ ዲጂታል በሆነ መንገድ እንዲከናወን ተደርጓል።
ይህም በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት በመመዝገብ መለያ ቁጥር ማግኘትና በአቅራቢያ በሚገኝ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሻራ መስጠትን ይጠይቃል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የዜጎችን ደህንነት በበለጠ ለመከታተል አሠራሮችን ዲጂታይዝ አድርጓል፡፡ በውጭ ሀገር የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን መረጃዎችን ማዕከል ባደረገ መልኩ ይመዘገባሉ።
በቴክኖሎጂ መተግበሪያዎች ዜጎች ለሥራ ወደ ውጭ ከመሰማራታቸው በፊት አስፈላጊውን መረጃ እንዲያገኙ፣ ስለ መብቶቻቸው እንዲያውቁና በውጭ ሀገር ችግር ሲገጥማቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በፍጥነት እንዲገናኙ እየተደረገ ነው።
ስምሪቱም በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ፈቃድ በተሰጣቸው ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በኩል ብቻ እንዲሆን ተሠርቷል፡፡
ለሥራ ስምሪት ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ የሚዘጋጅ ሰው በጤና ሚኒስቴር እና በመዳረሻ ሀገር በተመረጡ ጥራታቸው በተረጋገጠ የጤና ተቋማት የሕክምና ምርመራን በማድረግ፣ ሠራተኛው የሚሄድበትን ሀገር ቋንቋ ወይም ቢያንስ በሚገባው ቋንቋ የተዘጋጀውን የውል ስምምነት መረከብና መፈረም ይኖርበታል።
መንግሥት ከወሰዳቸው የሥራ ስምሪት ማሻሻያና የሪፎርም እርምጃዎች መሀከል ሁለተኛው ዜጎች በሚሰማሩባቸው እንደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሚሬቶች ፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ ዮርዳኖስ እና ሊባኖስ ካሉ ሀገራት ጋር በመደበኛነት የአሰሪና ሰራተኛ ስምሪት ስምምነት ተፈራርሟል።
ከዚህም ባለፈ የአውሮፓን የስራ ገበያ ለመቀላቀል ከጣልያን ጋር የሁለትዮሽ የሰው ኃይል ስምምነት ተፈጽሟል።
በሦስተኛ ደረጃ ዜጎች ከመሰማራታቸው በፊት የሙያና የክህሎት ስልጠናዎችን እንዲወስዱ በማድረግ በየዘርፉ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።
ይህም የጉልበት ሥራን ብቻ ሳይሆን የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ወደ ውጭ ሀገር እንዲላክ የሚያስችል አሠራር ነው።
ይህንን ዘርፍ ለማዘመንና አሠራሩን ግልጽ ለማድረግ መንግሥት ያደረገው አራተኛው ማሻሻያ ሕጋዊ አሠራሩን ማዘመን ነው፡፡
የወጡ የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሠራተኞች አዋጆች፣ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ታይተውና ሰልጥነው እንዲሰማሩ ያደርጋሉ።
የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አዋጅና አፈጻጸም መመሪያዎች ላይ በተደጋጋሚ በተደረጉ ማሻሻያዎች፣ የኤጀንሲዎች እንቅስቃሴዎች ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።
በጉዞ ወቅት በየሀገራቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የዜጎችን መብትና ደህንነት የመከታተልና የማስከበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እየተደረገ ነው።
ዜጎችም ከደላሎች አታላይ ወጥመድ ራሳቸውን በማዳን፣ ብቸኛውን ሕጋዊና አስተማማኝ መንገድ በየሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል በመመዝገብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግሥት አበክሮ ያሳስባል።

