Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ደንቢ ኢኮ ሎጅ የኢትዮጵያ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት መገለጫ     

default

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሏት የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ከግንባር ቀደምቶች ተርታ ትሰለፋለች።

እነዚህ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ሀብቶቿ ተገልጠው የቱሪዝም አቅም መሆን ሲገባቸው ተደብቀው ቆይተዋል።

ለዘመናት ሀብትን ካለመረዳት መስህቦቿ ውበታቸው ደብዝዞ፣ ከመሰረተ ልማት ተነጥለው ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ ከዓለም መቋደስ ያለባትን በረከት ማግኘት አልቻለችም።

መንግሥት የኢትዮጵያን መጻዒ ዕድል በመወሰን ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ በሚል ከለያቸው አምስት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምሰሶዎች መካከል ቱሪዝም አንዱ እንዲሆን በመወሰን የቱሪዝም አቅምን ለመጠቀም የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ባለፉት ዓመታት ተከናውነዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት፣ መሪነትና አስተባባሪነት ቱሪዝሙ እንዲጎለብት ያስቻሉ ስራዎች ተሰርተው አመርቂ ውጤት ተገኝቷል።

በዚህም በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ለዓለም ሳትገልጣቸው ሊከስሙ በቋፍ የነበሩ ውድ ሀብቶቿ ላይ ዳግም ህይወት የተዘራባቸው ድንቅ ስራዎች ናቸው፡፡

ከፕሮጀክቶቹ መካከል አንዱ በሆነው የገበታ ለትውልድ ቀደም ሲል የሀገሪቷ ገጽታ ላይ ብርሀን መፈንጠቅ ከጀመሩት የገበታ ለሸገርና ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች በመቀጠል ወደ ስራ የገባና በተለያዩ አካባቢዎች ተደብቀው የነበሩ ሀብቶችን የገለጠ ነው።

ይህ ፕሮጀክት በአስደናቂ ፍጥነትና ጥራት ተከናውነው ለአገልግሎት የበቁትን ደንቢ ኢኮ ሎጅ፣ የኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ፣ የሸበሌ ሪዞርት እና የሐይቅ ሎጎ ሪዞርት አካትቷል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ከተጀመሩት የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች መካከል በጥር ወር 2018 ዓ.ም ተመርቆ ወደ ስራ የገባው ደንቢ ኢኮ ሎጅ የመጀመሪያው ሲሆን፤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን በሚዛን አማን ከተማ አቅራቢያ ይገኛል፡፡

በ36 ነጥብ 7 ሄክታር ጥብቅ ደን ላይ የተፈጥሮ ግርማን ተጎናፅፎ የተንጣለለው ደንቢ ኢኮ ሎጅ፤ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ በዘላቂነት ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆን፤ ከዘርፉም የሚገኘውን ትሩፋት ከማሳደግ አንጻር የድርሻውን ይወጣል።

ፕሮጀክቱ በአካባቢው በሚገኙ ጥሬ ዕቃዎች እና በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች፣ በከፍተኛ ጥራት ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመሆን በመንግሥትና የግል ዘርፉ ትብብር የተገነባ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎች ታሪክ ውስጥ የጋራ ባለቤትነት ሞዴል የተተገበረበት ስራ ነው፡፡  

ይህ ስፍራ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የማረፊያ ክፍሎች፣ ዘመናዊና ባህላዊ ጥበብን በአንድ ያዋሀዱ መመገቢያ ስፍራዎችን ከሚያስደምም የኪነ-ህንጻ አሰራር ጋር አዋህዶ የአካባቢውን ማህበረሰብ ባህልና ሙዚቃን እያስተዋወቀ ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ እንግዶች በሩን ክፍት አድርጎ በሞገስ ተቀምጧል፡፡

ሎጁ ሙሉ በሙሉ ታዳሽ ኃይልን የሚጠቀም ሲሆን ይህም ሀገሪቷ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ጽኑ አቋም እንዳላት ይመሰክራል።

ከገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የደንቢ ኢኮ ሎጅ እንዴት የሀገርን የቱሪዝም መዳረሻዎች ተፈጥሮን እንደ ግብአት በመጠቀም ውብ ሀብትን መፍጠር እንደሚቻል አሳይቷል፡፡

ደንቢ ኢኮ ሎጅ የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት እውን ለማድረግ፤ ኢትዮጵያ የታደለቻቸውን እምቅ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶች በማልማት ወደ ፅኑ የኢኮኖሚ አለኝታነት መቀየር እንደሚቻል ማሳያ ቋሚ ምስክር ነው፡፡

በመልካም ፍቃዱ

Exit mobile version