Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

እንግሊዝ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፤ ቤልጂዬም ከሴኔጋል…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ እየተካሄደ በሚገኘው 23ኛው የዓለም ዋንጫ የ32 ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ፡፡
በዚህ መሰረትም የአፍሪካ አህጉር ተወካዮቹ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሴኔጋል 16ቱን ለመቀላቀል የሚፋለሙ ይሆናል፡፡
ምሽት 1 ሰዓት ላይ እንግሊዝ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአሜሪካ አትላንታ ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከፍተኛ ትኩረት ያገኘችው እንግሊዝ ጨዋታውን የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቷታል፡፡
በአንጻሩ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በምድብ ጨዋታዎች ባሳየችው ድንቅ አቋም ለእንግሊዝ ብርቱ ፈተና እንደምትሆን ይጠበቃል፡፡
የዚህ ጨዋታ አሸናፊም በቀጣይ ዙር ሩብ ፍጻሜውን ለመቀላቀል ስኬታማ ጉዞ ላይ የምትገኘውን አዘጋጇን ሀገር ሜክሲኮን ይገጥማል፡፡
በሌላ በኩል ምሽት 5 ሰዓት በሲያትል ከተማ ቤልጂዬም ከሌላኛዋ የአፍሪካ ተወካይ ሴኔጋል ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡
ሴኔጋል በምድብ ጨዋታዎች ኖርዌይ እና ፈረንሳይን በብርቱ ፈትና የተሸነፈች ቢሆንም ኢራቅን በሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ በጥሩ ሶስተኝነት ጥሎ ማለፉን መቀላቀሏ ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም ሌሊት 9 ሰዓት አዘጋጇ ሀገር አሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ላይ ጥሩ ሶስተኛ በመሆን ወደ ጥሎ ማለፉ ያለፈችውን ቦሲኒያ ሄርዞጎቪና ታስተናግዳለች፡፡
አሜሪካ በምድብ ጨዋታዎች ቀድማ መሰናበቷን ባረጋገጠችው ቱርኪዬ ከመሸነፏ ውጪ ሁለቱን ጨዋታዎች በብቃት ማሸነፏ የዛሬው ጨዋታ እምብዛም እንደማይከብዳት ተገምቷል፡፡
ቦሲኒያ ኳታርን በማሸነፍ ወደ ጥሎ ማለፉ የተቀላቀለች ሲሆን÷ በዛሬው ጨዋታ ለአሜሪካ ብርቱ ፈተና በመሆን እድሏን ለመሞከር ወደ ሜዳ ትገባለች፡፡
Exit mobile version