Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በቬንዙዌላ የርዕደ መሬት አደጋ ከስድስት ቀናት በኋላ የሶስት ዓመት ህጻን በህይወት ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቬንዙዌላ በደረሰው አስከፊ የርዕደ መሬት አደጋ ከስድስት ቀናት በኋላ የሶስት ዓመት ህጻን ልጅ ከፍርስራሽ ውስጥ በህይወት ተገኝቷል።

የነፍስ አድን ሰራተኞች አሁንም የአደጋው ተጎጂዎችን ለመታደግ ጥረት እያደረጉ ይገኛል።

በዚህ ጥረት ከስድስት ቀናት በኋላ ክሊበር ሞራን የተባለ ህጻን ልጅ በላጉዌራ ግዛት በፍርስራሽ ውስጥ የተገኘ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ደረጃ ዕርዳታ ሕክምና ተደርጎለት ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ህጻኑ በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የህጻኑ በህይወት መገኘት ለህዝባችን ተስፋ ነው ብለዋል።

በፍርስራሽ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በህይወት የማውጣት ዕድል እንዳለ ጠቅሰው፤ የነፍስ አድን ስራው እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ ባለፈው ሳምንት በተከሰተው ርዕደ መሬት የሟቾች ቁጥር 1 ሺህ 943 ደርሷል።

ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም።

የ ናሳ የሳተላይት መረጃ የመጀመሪያ ግምገማ እንደሚያሳየው ግዙፉ መንቀጥቀጡ 58 ሺህ 870 ህንፃዎችን ማውደሙን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) እንዳስታወቀው፤ በአደጋው የምግብ እጥረት መስፋፋቱን፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች መቆማቸውን እና የግንኙነት መስመሮች ተቋርጠዋል።

በርካቶች አስቸኳይ ምግብ እና መጠለያ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጾ፤ በርዕደ መሬቱ ለተጎዱ ሰዎች ጊዜያዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።

ከትናንት በስቲያ ከተከሰተው አስከፊ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ እናት እና የ18 ቀን ጨቅላ ልጇ በህይወት መትረፋቸው መገለጹ ይታወሳል።

በትዕግስት ግዛቸው

Exit mobile version