የገጠር ኮሪደር ልማት በኢትዮጵያ የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በከፍተኛ ደረጃ ለመለወጥና ከተሜነትን ወደ ገጠር ለማስፋፋት የተጀመረ ሀገራዊ የልማት ሪፎርም ነው፡፡
ይህ ፕሮጀክት በከተሞች የታየውን አመርቂ የኮሪደር ልማት ውጤት ወደ ገጠሩ ማህበረሰብ በማስፋፋት፣ የእያንዳንዱን አርሶ አደር ቤት፣ ግቢና አጠቃላይ የኑሮ ሁኔታ ማዘመን ላይ ያተኩራል፡፡
ዋና ዓላማውም በገጠርና በከተማ መካከል ያለውን የዕድገት ልዩነት በማጥበብ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት መቀነስና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ ነው፡፡
ይህ ዘመናዊ የልማት ሥራ በአራት ዋና ዋና ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ ይንቀሳቀሳል፡፡
የመጀመሪያው ሞዴል መንደሮችን መገንባት፣ የመኖሪያ ቤቶችን ማሻሻል፣ ለአርሶ አደሩ ምቹ፣ ንጹህና ሰብአዊ ክብርን የሚመጥኑ ዘመናዊ ቤቶችን በአካባቢ ግብዓቶች መገንባት ነው፡፡
ይህም የቤትና የአካባቢ ንጽህናን ማሻሻል፣ ዘመናዊ የሽንት ቤትና የመታጠቢያ ክፍሎች ግንባታን ያካትታል።
የገጠር መንገዶችን በማስፋፋት፣ አረንጓዴ ስፍራዎችን በመፍጠርና በታዳሽ ኃይል አጠቃቀም ረገድ የጎላ ጠቀሜታም አለው።
የሰዎችና የእንስሳት መኖሪያን መለየት ሁለተኛው የገጠር ኮሪደር ልማት ምሰሶ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረውን ከብቶችና ሰዎች በአንድ ጣሪያ ስር የመኖር ልምድ በመለወጥ፣ የከብቶች መኖሪያ ወይም በረትን ከሰው መኖሪያ ቤት ለይቶ ንጽህናውን በጠበቀ መልኩ ማዘጋጀትን ያካትታል።
ከብቶች ከሰው መኖሪያ በመለየታቸውና የንጹህ ውኃና ሳኒቴሽን መሠረተ ልማቶች በመዘርጋታቸው በንጽህና ጉድለት የሚመጡ በሽታዎችን ይቀንሳል።
የታዳሽ ኃይል አጠቃቀምን ማስፋፋት ሌላኛው ምሰሶ ነው፡፡
ይህም ለአርሶ አደሩ ቤቶች የሶላር ኃይል መግጠም እና ከእንስሳት እዳሪ የሚመነጭ የባዮ ጋዝ ማብሰያ ሥርዓት መዘርጋትን ያካትታል።
የቤት ውስጥ የአየር ብክለትንና የሴቶችን የእንጨት ፍለጋ እንግልትንም ያስቀራል።
የሌማት ትሩፋት ትስስርን መፍጠር አራተኛው ምሰሶ ሲሆን፣ በአርሶ አደሩ ግቢ ውስጥ የጓሮ አትክልት ስፍራ፣ የንብ ቀፎዎች፣ የዶሮ እርባታና የወተት ላሞችን ማደራጀትን ያካትታል።
ይህም ለቤተሰብ የተመጣጠነ ምግብ ከማቅረብ ባለፈ ተጨማሪ ገቢ ያስገኛል።
አርሶ አደሩ በግቢው ውስጥ በሚያመርታቸው የፍራፍሬ፣ ማር፣ እንቁላልና ወተት ምርቶች የራሱን ፍጆታ አሟልቶ ለገበያ በማቅረብ የገቢ አቅሙን ያሳድጋል።
ይህ የኮሪደር ልማት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነትና ክትትል በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በተግባር ተጀምሮ አመርቂ ውጤቶች እየታዩበት ይገኛል።
በአጠቃላይ የገጠር ኮሪደር ልማት የገጠሩን ማህበረሰብ አስተሳሰብና የኑሮ ዘይቤ በመለወጥ፣ የኢትዮጵያን የገጠር መንደሮች ውብ፣ ንጹህና ለኑሮ ተስማሚ የማድረግ ትልቅ ሀገራዊ ራዕይ ነው።

