Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሚቀጥሉት አስር ቀናት ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሚቀጥሉት አስር ቀናት በክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል አለ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት።

በሚቀጥሉት አስር ቀናት በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜንና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ ሁኔታ በመጠንም ሆነ በሥርጭት እየተስፋፋ እንደሚሄድ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡

ይህም የአፈር ውስጥ ርጥበትን የሚያሻሻል ከመሆኑ አንጻር ዘር ለመዝራት አስቀድመው ለተዘሩና በተለያዩ እድገት ደረጃ ላይ ላሉ ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎችና የጓሮ አትክልቶች አዎንታዊ ፋይዳ እንዳለው ጠቁሟል።

የመኸር ሰብል አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖረውን መልካም አጋጣሚ መጠቀምና አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ የሚያስችሉ ጥንቃቄዎችን ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝቧል፡፡

የገጸ ምድር የውሃ ሽፋን በአብዛኛው ተከዜ፣ መረብ፣ አባይ፣ ባሮ አኮቦ፣ የላይኛውና መካከለኛ ኦሞ፣ ጊቤ ስምጥ ሸለቆ እና የአዋሽ ተፋሰሶች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው የገጸ ምድር ውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸው ተመላክቷል፡፡

እንደ ኢንስቲትዩቱ ገለጻ፥ በላይኛውና መካከለኛው ገናሌ ደዋ፣ ዋቤ ሸበሌ እንዲሁም በኦጋዴን ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እስከ መካከለኛ የሚደርስ የገጸ ምድር ውሃ ፍሰት ይኖራቸዋል፡፡

ይህ የዝናብ ሁኔታ የጎርፍ ክስተት፣ የመሬት መንሸራተትና የወንዞች ሙላት ሊያስከትል እንደሚችል የገለጸው ኢንስቲትዩቱ፥ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እንዲከናወኑ ማሳሰቡን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version