አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ ኢትዮጵያ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በፅናት የሚያሻግሩ ተተኪ ጀግኖች እየፈጠረች ነው አሉ።
ሌተናል ጄኔራሉ በብላቴ ልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል በመገኘት የ45ኛ ፅናት ኮርስ ሰልጣኞችን የስልጠና ሁኔታና የመሠረተ ልማት ግንባታ ዝርጋታ ጎብኝተዋል።
በቆይታቸውም ከአመራሮች፣ አሰልጣኞች እና ሰልጣኞች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በዚህ ወቅትም ዕዙ በግዳጅ ቀጠና ሁሉ የሕዝብን ሰላም በማረጋገጥ፣ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመጠበቅ እና ሸኔና ፅንፈኛ ቡድኖችን በመምታት አጥጋቢ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
ዕዙ ሕዝባዊ ባህሪውን ተላብሶና በቴክኖሎጂ ዘምኖ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጠና ሁሉ የሀገርን ሰላም በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
የፅናት ኮርስ ሰልጣኞች የቀይ መለዮ ባለአደራና ተተኪ መሆናቸሁን ተገንዝባችሁ ቀሪ የስልጠና ጊዜያችሁን በእልህ፣ በወኔ፣ በጀግንነት እና በታታሪነት መከታተል ይገባችኋል ማለታቸውንም የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
የዕዙ ም/አዛዥ ሜ/ጄ አበባው ሰይድ በበኩላቸው÷ ዕዙ ማንኛውም ፈተና ሳይበግረው አኩሪ የጀግንነት ገድል እየፈፀመ መሆኑን ገልጸው÷ ሰልጣኞች ይህንን አደራ ለማስቀጠል ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

