Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኮሪደር ልማት የመደመር ትሩፋት፣ ከከተማ እስከ ገጠር

በኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞችና በገጠር አካባቢዎች እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማት፣ የዜጎችን የመኖርያና የሥራ አካባቢ ደረጃ በማሻሻል ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ-ምህዳራዊ ለውጥ ማምጣት ያስቻለ ታላቅ ሀገራዊ የሪፎርም ፍሬ ነው።

ይህ የመደመር እሳቤ የልማት ስትራቴጂ ከውበትና መሠረተ ልማት ግንባታ ባለፈ የዜጎችን ክብርና የዕለት ተዕለት ሕይወት በማሻሻል ረገድ በርካታ ተጨባጭ ትሩፋቶችን አስገኝቷል፡፡

ያለፈውን መልካም ዕሴት ጠብቆ፣ የዛሬውን አሻሽሎና የወደፊቱን አርቆ በመመልከት ሀገራዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ የመደመር እሳቤ ዋነኛው ምሰሶ ነው፡፡

በዚህ እሳቤ የተወለደው የኮሪደር ልማት፣ የከተማና የገጠር የልማት ስብራትን በመጠገን የዜጎችን የኑሮ ክብር ከፍ ያደረገ ሁለንተናዊ ንቅናቄ ሆኗል።

ይህ ታላቅ ፕሮጀክት በዋና ዋና ከተሞች ተጀምሮ አሁን ላይ እስከ ገጠር መንደሮች ድረስ በመዝለቅ ተጨባጭ ውጤቶችን አስገኝቷል።

የከተማውን የኮሪደር ልማት ስንመለከት ለተሸከርካሪዎች ብቻ ሳይሆን ሰፋፊ የእግረኛ መሄጃዎችን፣ የብስክሌት መስመሮችን እና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ መንገዶችን በማካተቱ ለሰው ልጅ ቅድሚያ የሚሰጥ ሰው ተኮር መሠረተ ልማት ስለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

ዘመናዊና ወጥ የሆኑ የጎዳና ላይ መብራቶች በመገጠማቸው፣ ከተሞች በምሽትም ጭምር ደህንነታቸው ተጠብቆ ንቁ የንግድ እንቅስቃሴን እንዲያስተናግዱ አስችለዋል።

እንደ መጽሐፍና ጋዜጣ ሻጮች፣ ጫማ ጠራጊዎችና አነስተኛ ነጋዴዎች ከአቧራና ከፀሐይ ተጠልለው የሚሰሩባቸው ውብ ኪዮስኮች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የሕዝብ መጸዳጃና መታጠቢያ ቤቶችም ተገንብተዋል።

ነዋሪዎች ያለምንም ክፍያ የሚዝናኑባቸውና የሚያነቡባቸው አረንጓዴ ፓርኮች፣ የውሃ መዝናናዎች እና ለታዳጊዎች የሚሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች ተስፋፍተዋል።

የመደመር ፍልስፍና በከተማ ብቻ አያበቃም፡፡ የከተማና የገጠር የኑሮ ልዩነትን በማጥበብ ያምናል። የኮሪደር ልማቱ በፍትሐዊ የልማት ስርጭት ወደ ገጠር በመሻገሩ የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን መንደሮች ገጽታ መቀየር ጀምሯል።

ለዚህም ነው ሞዴል መንደሮችን በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል እየገነባ ያለው፡፡ ሞዴል የገጠር ኮሪደር መንደር በኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ የሚገኘው የገጠር ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ አካል ነው።

እስካሁን ከተገነቡት ለምሳሌ ያህል ለማየት የሀማሳ ሞዴል መንደር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የሾምባ ኪጭብ ሞዴል መንደር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እና የዋራበት ጫማ ሞዴል መንደር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተገንብተው ነዋሪውን ተጠቃሚ አድርገዋል፡፡

እነዚህ መንደሮች አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ካልተደራጀና ተበታትኖ ከሚኖርበት ባህላዊ አኗኗር በማውጣት፣ መሰረተ ልማት ወደተሟላላቸው ዘመናዊ፣ ፅዱ እና ምርታማ የጋራ መንደሮች የማሰባሰብ የመደመር ፍልስፍና ፍሬዎች ናቸው።

በገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩ ሕይወት እየዘመነ ነው፡፡ አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆኑበት፣ የእንስሳት ማደሪያ፣ የባዮ ጋዝ፣ የንብ ቀፎ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እና ዘመናዊ የመታጠቢያ ክፍሎችን ያሟሉ አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶች ተገንብተውላቸዋል።

ኮሪደር ልማቱ የከተማና የገጠር ኢኮኖሚያዊ ትስስርን እየፈጠረ ይገኛል፡፡
ከገጠር እስከ ከተማ የተዘረጉት የኮሪደር መንገዶች አርሶ አደሩ ምርቱን በፍጥነትና በቅናሽ ዋጋ ወደ ከተማ ገበያ እንዲያቀርብ ምቹና ቀልጣፋ የገበያ ትስስር ፈጥረዋል።

በከተሞችም ሆነ በገጠር አካባቢዎች የተሰሩት የኮሪደር ልማቶች፣ የወንዝ ዳርቻ ልማቶችና አረንጓዴ ስፍራዎች የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪዝምን በእጅጉ አሳድገዋል።

በአጠቃላይ የኮሪደር ልማት፣ ከተሞችንና የገጠር መንደሮችን እያስተሳሰረ ያለ ሲሆን፣ የሰውን ልጅ ክብር፣ ጤና እና ሁለንተናዊ ብልጽግናም ማረጋገጥ እየቻለ ነው፡፡

Exit mobile version