Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያውያንን ክብር ያስቀደመው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ …

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መሰረት የሆነው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደህንነት እና ክብራቸውን ያስጠበቀ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል፡፡

ከለውጡ በፊት ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ በውጪ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ጨምሮ ለበርካታ ችግሮች እና ጫናዎቸ ሲዳረጉ ቆይተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት መንግሥት ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሰጠው ትኩረት ከተለያዩ ሀገራት ጋር በቅርበት በመስራት በስደት ወይም በህጋዊ ሥራ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር እና ደህንነታቸው እንዲረጋገጥ ማድረግ ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን እንደ አንድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አድርጋ መተግበር ከጀመረች ወዲህ ከወትሮው በተለየ መልኩ እያንዳንዱን ዜጋ የሀገሩ አምባሳደር እንዲሆን ያደረገ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል፡፡

ለአብነትም በዲፕሎማሲው አማካኝነት በውጭ ሀገር የሚሰሩ ዜጎችን መብት ለማስከበር ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ከኳታርና ከጆርዳን መንግሥታት ጋር የሁለትዮሽ የሰራተኛ ስምምነት ተፈርሟል።

ይህም ዜጎች በህጋዊ መንገድ እንዲቀጠሩ፣ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰንላቸውና የህክምና ዋስትና እንዲኖራቸው አስችሏል።

በተጨማሪም መንግስት ባካሄደው መጠነ ሰፊ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በሳዑዲ አረቢያ በችግርና በእስር ላይ የነበሩ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው መመለስና ማቋቋም ተችሏል፡፡

በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ዜጎችን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በኒው ደልሂ በነበረው የብሪክስ ሀገራት ሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ የደቡብ አፍሪካ አቻቸው ሮናልድ ላሞላን አግኝተው ማነጋገራቸው ይታወሳል፡፡

በዚህም በደቡብ አፍሪካ በተቀሰቀሰው አመፅ ሳቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደረሰውን ጥቃት በጋራ ለመከላከል የሚያስችል ውይይት ተደርጓል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ደህንነት በጋራ ለማስጠበቅ የኢትዮጵያ ልዑክ በቅርቡ ወደ ደቡብ አፍሪካ መሄዱ እና ሌሎች ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መደረጋቸው ይታወሳል፡፡

በአጠቃላይ መንግሥት ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የሰጠው ትኩረት በመንግስትና በውጭ በሚኖሩ ዜጎች መካከል ያለውን መተማመን ያሳደገ ሲሆን፤ የዳያስፖራው የሀገር ውስጥ ሁለንተናዊ ተሳትፎ አድጓል፡፡

በዚህም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ያላቸው ድጋፍ ተጠናክሯል፡፡

በአቤል ነዋይ

Exit mobile version