አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትን ህይወት ለማሻሻል የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባዋ በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ግንባታን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፥ የመኖሪያ መንደሩ ባለ 15 ፎቅ 12 ህንፃዎችን ያካተተ ነው፡፡
የፖሊስ ሰራዊቱ በሕዝብ የተጣለበትን አደራ በአግባቡ እንዲወጣ የሰራዊቱን መንደር እንገነባለን ብለን የገባነውን ቃል ዛሬ ወደ ተግባር አሸጋግረነዋል ብለዋል፡፡
ሰራዊቱ የአፍሪካ እንዲሁም 3ኛዋ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባ ከተማ የሚያገለግል መሆኑን ያወሱት ከንቲባዋ፥ የመኖሪያ መንደሩ ሰራዊቱ በትጋትና በአግባቡ ሕዝቡን እንዲያገለግል ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም የሰራዊቱን አባላት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ለመቀነስ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
ተቋሙን በእውቀትና በቴክኖሎጂ ለማስታጠቅ እንዲሁም የሰራዊቱን አባላት ህይወት ለማሻሻል በከፍተኛ ትጋት የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

