አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የክረምት ወራትን የዝግጅት ምዕራፍ ሳይሆን የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና ኢኒሼቲቭ ሥራዎችን ያለማቋረጥ በመፈጸም በትኩረት እየተሠራ ነው አሉ የአማራ ክልል የከተማ ክላስተር አስተባባሪ አህመድ መሀመድ (ዶ/ር)።
አስተባባሪው እንዳሉት÷ የተካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ ለሕዝቡ ጥያቄ በውጤትና በአገልግሎት ምላሽ ለመስጠት ያለምንም እረፍት መሥራት ያስፈልጋል።
በአብዛኛው በከተሞች ላይ የሚከናወኑ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የምርታማነት፣ የንግድና የሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባራትን ለማስቀጠል የተቀናጀ የጋራ ስምሪትና የአመራር ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ሀገር የተጀመሩ ትላልቅ ኢኒሼቲቮችን ወደ ተሻለ ውጤት ለመቀየርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማረጋገጥ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን አስተባባሪው ጠቁመዋል።
በዚህም የገጠርና የከተማ ኮሪደር ልማትን ጨምሮ በኮደርስ፣ በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያና በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተጀመሩ ሥራዎችን በሰፊውና በዘላቂነት ለማስቀጠል እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ስቡህ ገበየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በ2019 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 1 ሚሊየን የሚሆን የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ በክረምቱ 90 ቀናት 119 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ይህ የሥራ ዕድል የገበያ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ እንዲሆን የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ክህሎት መር፣ ተወዳዳሪና ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው አብራርተዋል።
በ5 ሚሊየን የኮደርስ ፕሮግራም ላይ ያለው አፈጻጸም ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር ወደ 173 በመቶ ማደጉን እና በዚህ ክረምት የ200 በመቶ የመፈጸም ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ያመለከቱት ደግሞ የአማራ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ የቻለ ይግዛው ናቸው።
በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ እስካሁን ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዜጎች ባለቤት መሆን መቻላቸውን ገልጸው፤ በቀሪ የክረምት ወራትም በክልሉ የሚገኙ ዜጎችን የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ በተቀናጀ መልኩ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም የአመራር አካላትና የሚመለከታቸው የትምህርትና የቴክኖሎጂ ተቋማት የተቀናጀ የጋራ ስምሪትን በመከተል፣ የተያዙ የልማት ግቦች እንዲሳኩና የኢኮኖሚ ሽግግሩ እንዲፋጠን በቁርጠኝነት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በዮናስ ጌትነት

