አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአርባ ምንጭ ከተማ የተገነባው ኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ የግሉ ዘርፍ ማበርከት የሚችለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በግልጽ የሚያሳይ ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በአርባ ምንጭ ከተማ በ52 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈውን የኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በውስጡ 53 ቅንጡ ቪላዎችን ያካተተ ሲሆን፥ ከ300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተመላክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ አርባ ምንጭ የልማት ምንጭነቷ እየጎመራ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
መሰል ኢንቨስትመንቶች የመደመር መንግሥት የገነባቸውን መሠረተ ልማቶች ተከትሎ የግሉ ዘርፍ ማበርከት የሚችለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በግልጽ ያሳያሉ ነው ያሉት፡፡
የሀገራችንን የቱሪዝም አቅም ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ መሰል ታላላቅ ፕሮጀክቶች ላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በስፋት እንዲሰማሩና መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

