ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት አንዷ ነች፡፡
ነገር ግን አሁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አያገኙም።
ይህንን መሰረታዊ ክፍተት ለመሙላት እና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር ለመቀየር መንግሥት በመደመር እሳቤ የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን መርሃ ግብር በመቅረጽ በታዳሽ ኃይል ላይ የተመሰረተ ሰፊ ስራ እየሰራ ይገኛል።
ይህ ስትራቴጂ እጅግ ሰፊ የሆነውን የሀገሪቱን የተፈጥሮ ፀጋ በመጠቀም ንጹህ ኃይልን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ነው።
ኢትዮጵያ በኃይል አቅርቦት ራሷን ለመቻል በየዘመናቱ ከፍተኛ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡
በዚህም ከአባ ከሳሙኤል፣ ቆቃ፣ ጊልገል ጊቤ 2፣ ጊልገል ጊቤ 3፣ ኮይሻ፣ ጣና በለስ፣ ተከዜ፣ ገናሌ ዳዋ 3፣ ሕዳሴ ግድብ እና ከመሳሰሉት ኃይል ታመነጫለች፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ90% በላይ የሚሆነው የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚመነጨው ከውኃ ነው።
በአዳማ፣ አሸጎዳ እና መቐለ አካባቢዎች የሚገኙት የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች የውኃ እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት የኃይል አቅርቦቱን ለማረጋጋት ትልቅ እገዛ እያደረጉ ነው።
ከዋናው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ርቀው ለሚገኙ የገጠር ማህበረሰቦች የፀሐይ ኃይል ፈጣን እና ወጪ ቆጣቢ መፍትሔ ሆኖ እያገለገለ ነው።
በአሁኑ ወቅት ከጠቅላላው የኃይል ተጠቃሚ ውስጥ 35.7% ያህሉ ከዋናው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ውጪ የሶላር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን ችሏል።
በተጨማሪም በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የሚገኘውን ከፍተኛ የከርሰ ምድር እንፋሎት የሙቀት ኃይል በመጠቀም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበግር የኃይል አማራጭ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለውን የ65% አጠቃላይ የኃይል ተደራሽነት ምጣኔ ወደ 100% ለማሳደግ እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት በርካታ ስልቶችን ተግባራዊ እያደረገች ነው፡፡
የጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የትኞቹ አካባቢዎች በዋናው መስመር፣ በንዑስ ማከፋፈያዎች ወይም በተናጠል የሶላር ሲስተም መሸፈን እንዳለባቸው በበጀት ቆጣቢ የተቀናጀ የኃይል አቅርቦት እቅድ እየለየች ለተደራሽነቱ እየሰራች ትገኛለች፡፡
በመደመር መርህ መንግሥት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲኖረው እያበረታታ ያለ ሲሆን፣ በዚሁ ላይ የፖሊሲ ማሻሻያዎችንም አድርጓል፡፡
በዚህም መንግሥት በኃይል ማመንጨት ስራ ላይ የነበረውን ብቸኛ ተሳትፎ በማላላት፣ የግል ባለሀብቶች በመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት መርሃ ግብር አማካኝነት በታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ በህግ ፈቅዷል።
እስከ አሁን በዘርፉ የተሰራው ሥራ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አዳዲስ ቤተሰቦችን ከዋናው መስመር ጋር በማገናኘት እና ተቋማዊ አቅምን በመገንባት ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ይህ ሥራ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የታዳሽ ኃይል ተደራሽነት መስፋፋት በቀጥታ ከሀገሪቱ የረጅም ጊዜ የዕድገት ግቦች ጋር የሚያያዝ ነው፡፡
ለገጠር ጤና ጣቢያዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና አነስተኛ የግብርና ማቀነባበሪያዎች የኃይል አቅርቦት ማግኘት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ይለውጣል።
አስተማማኝ እና ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ለሀገር ውስጥ አምራቾች መኖሩ ለሀገራዊ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚኖረው ሚና የጎላ ነው፡፡
ከዚህ በዘለለም ኢትዮጵያ በምታመነጨው ታዳሽ ኃይል ቀጣናዊ ትስስር እና አረንጓዴ ዲፕሎማሲን እየተገበረች ስለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ንጹህ ኃይል ለኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን በመሸጥ ምስራቅ አፍሪካን በታዳሽ ኃይል ለማስተሳሰር እየሰራች ነው፡፡
ይህ አካሄድ በዓለም አቀፍ ደረጃ አየር ንብረትን የማይበክል የልማት መንገድ በመከተል የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ መሪነቷን ያሳያል።
የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ተደራሽነት ጉዞ ፈታኝ ቢሆንም፣ የተቀረጹት ዘመናዊ የመደመር ስልቶች እና የተጀመሩት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ብርሃን እየመሯት ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች የሀገሪቱን ብርሃን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የተጣሉ ጠንካራ መሠረቶች ናቸው።
በዘርፉ የግሉን ተሳትፎ ይበልጥ በማጠናከር እና የፋይናንስ አቅምን በማሳደግ፣ ኢትዮጵያ እስከ 2035 ድረስ መላውን ማህበረሰብ የንጹህ ኃይል ተጠቃሚ የማድረግ ራዕይዋን ማሳካት የምትችልበት ዕድል ሰፊ ነው።
በቀጣይም በግንባታ ላይ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን የኃይል መሪነት ይበልጥ እንደምታጠናክር ይታመናል።
ኑ፤ ሀገር እንሥራ!

